በቀድሞ መንግስት ምርኮኛ ወታደሮች የተመሰረተው ኦህዴድ የ25 ዓመት የምስረታ በዓሉን ሊያከብር ነው

የካቲት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀድሞ የደርግ ወታደሮችን በማሰባሰብ  በህወሓት በጎ ፈቃድ የተመሰረተው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የተመሠረተበትን 25 ዓመት በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

የኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳባ ደበሌ  በሰጡት መግለጫ ኦህዴድ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ከመጋቢት 1 እሰከ መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በልዩ ልዩ መርሃግብሮች ያከብራል፡፡

በወጣው ፕሮግራም መሰረትም ከመጋቢት 1  እስከ 16 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ህዝባዊ ንቅንቄ ለማድረግ ያስችላሉ የተባሉ የፓናል ውይይቶች፣ ሕዝባዊ ሰልፎች እንደሚካሄዱና መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም ዋናው በዓል እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞ  የህወሓት  ከፍተኛ  አመራርና ታጋይ የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፍ ህወሓት በጫካ በነበረበት ወቅት እንደኦነግ ካሉ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ግንባር ለመመስረት የነበረው ፍላጎት ባለመሳካቱ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በሻዕቢያ ተማርከው መንገድ ሲያሰራቸው የነበሩትን  የኦሮሞ  የቀድሞ  ወታደሮችን  ወደ ማሰባሰቡ ፊቱን ማዞሩን  አስረድተዋል፡፡ እነዚሁ ምርኮኛ የቀድሞ መንግስት ወታደሮች  አንዳንዶቹ ኢህዴን  እየተባለ በሚጠራው ድርጅት ታቅፈው እንደነበርም ያስታወሱት አቶ ገብሩ  ፣ እነዚህኑ ንቁና ዝግጁ የሆኑ ወታደሮች በማሰባሰብ የህወሓትን ፕሮግራም በመያዝ  በ1982 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ውስጥ ደራ አካባቢ ኦህዴድ መመስረቱን  አስታውሰዋል፡፡

ኦህዴድን በማቋቋም ረገድ ግንባር ቀደም ከነበሩት መካከል ኩማ ደመቅሳ በቀድሞ ስሙ ታዩ በአሁኑ ወቅት በአምባሳደርነት የተሾሙ፣ ኢብራሂም  መልካ ከድርጅቱ  ተሰናብተው  ነጋዴ  የሆኑ ፣ አባዱላ  ገመዳ  የፓርላማ አፈጉባዔ የሆኑ፣ ባጫ ደበሌ  የመከላከያ ጄኔራል  የነበሩና በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙ የሚጠቀሱ መሆናቸውን አቶ ገብሩ «ሉአላዊነትና ዴሞካራሲ በኢትዮጵያ» በሚል ስም በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡

ህወሓት የተመሰረተበትን 40ኛ  ዓመት  በመቶ  ሚሊዮኖች  የሚቆጠር  ገንዘብ በመከስከስ  ከአንድ  ወር  በላይ  ሲከበር  የቆየ  ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የኦህዴድ 25ኛ ዓመት በዓል ከፍተኛ ገንዘብ ፈሶበት እንዲከበር የተወሰነው እግረመንገድ አጋጣሚውን ለምርጫ ቅስቀሳ ለመጠቀም እንደሚመች መሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እየተናገሩ ነው፡፡ ይህ በመንግስት ሐብትና ገንዘብ ለአንድ ፓርቲ የሚደረግ የምርጫ ቅስቀሳ ሕገወጥ መሆኑንም እነዚሁ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡