በሽንሌ ዞን አብዲ ኢሌ ያዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ከሸፈ

በሽንሌ ዞን አብዲ ኢሌ ያዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ከሸፈ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ/ም) የአቶ አብዲ ኢሌን አገዛዝ በኢትዮ-ሶማሊ ክልል እየፈጸመ ያለውን ግድያ፣ እስርና ሌሎችም ኢ ሰብአዊ ድርጊቶች በመቃወም ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ከተካሄዱ በሁዋላ፣ ፕሬዚዳንቱ በሽንሌ ከተማ ያዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ሳይስካለት ቀርቷል። ህዝቡ በሰልፉ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከተለያዩ አካባቢዎች የሰበሰባቸውንና በመኪና ጭኖ ያመጣቸውን እንዲሁም የልዩ ሃይሉን ሚሊሺያዎች የሲቪል ልብስ በማስለበስ በከተማው መሃል ሰልፍ እንዲያደርጉና ድጋፋቸውን እንዲገለጹ ለማድረግ ሞክሯል። ድርጊቱ ብዙዎቹን የከተማዋ ነዋሪዎች ያስገረመ ሲሆን፣ አብዲ ኢሌ ተስፋ እየቆረጠ ሲመጣ የፈጸመው ድርጊት ነው ብለውታል።
በውጭ አገር የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ሰሞኑን የአብዲ አሌ አገዛዝ በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል በማውገዝ መግለጫ አውጥተው ነበር።
ተቃውሞው አድማሱን እያሰፋ ሊሄድ ይችላል በሚል ፍርሃት አብዲ ኢሌ የልዩ ሃይል አባላን ከየቦታው እየሰበሰበ ነው። ኦህዴድ እና አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ከጀርባ ሆነው በክልሉ ተቃውሞ እንዲነሳ እያሴሩብኝ ነው በማለት አብዲ አሌ ለሚቀርባቸው ሰዎች እየተናገረ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። እነ ለማ መገርሳ እሱን ለማውረድ ከጀርባ እቅድ የሚነድፉ ከሆነ እሱን በኦሮምያ መረጋጋት እንዳይኖረ እንደሚሰራ እየተናገረ ያለው አቶ አብዲ ኢሌ፣ በተለይም የኦህዴድን አጀንዳ ያስፈጽማሉ የሚላቸውን ሰዎች እየወነጀለ ለማሰር እንቅስቃሴ መጀመሩን ምንጮች ይገልጻሉ።