በሽንሌ ዞን በህዝቡ ላይ የሚደርሰው ጥቃት መጨመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 13 ቀን 2010 ዓ/ም ) ላለፉት 5 ወራት በሺንሌ ዞን የተጀመረው ተቃውሞ እየቀጠለ ባለበት ሰዓት ፣ የአብዲ ኢሌ አስተዳደር የሚወስደውም እርምጃ በተመሳሳይ መልኩ እየጨመረ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ሻለቃ አሊ ሳምሪ ሰገድ እንደተናገሩት ከ3 ቀናት በፊት አዲጋላ ላኢ አንዲት ሴት መገደሏንና ሌላ ሴት ደግሞ መቁሰሏን ተናግረዋል። መንግስት ጣልቃ ቢገባም እስካሁን ጣልቃ አለመግባቱን ገልጸዋል።
አቶ አብዲ አሌ ከክልላቸው አልፎ አልፎ በፌደራል ደረጃ እርሳቸውን በሚቃወሙአቸውን ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም እያደረጉ ነው። በርካታ ታዋቂ ምሁራንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አሁንም ድረስ በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በቅርቡ የሶማሊ ክልል የአገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው የሰጡትን ቃለ ምልልስ አቶ አብዲ አሌ በወኪሎቻቸው አማካኝነት እንዳይተላለፍ ማስደረጋቸውን ኢሳት ከታማኝ ምንጮች ለማረጋገጥ ችሎአል። ድርጊቱ የክልሉን ተወላጆች እያስቆጣ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አቶ አብዲ ኢሌ ከስልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቁ የመብት ታጋዮች፣ የዶ/ር አብይ መንግስት በክልሉ ለሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጆሮ አልሰጠም በሚል መተቸት ጀምረዋል።