በሽብር ወንጀል በተከሰሱት በእነ አቶ አንዱአለም አራጌ ላይ ነገ ፍርድ ይሰጣል

ሰኔ አስራ ሦስት ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፣  ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማህበረሰብ አባለት በነገው እለት የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጣቸው ሲሆን ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ የፖለቲካ አጋሮቻቸው ከፍርድ ቤቱ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

በእነ አንዱአለም አራጌ የክስ መዝገብ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አንዱአለም አራጌ እና አቶ ናትናኤል መኮንን፣ የመኢዴፓ አመራር የሆኑት አቶ  ክንፈ ሚካኤል ደበበ፣ እንዲሁም አቶ የሽዋስ ይሁንአለም፣ ዮሀንስ ተፈራ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና  አንዱአለም አያሌው ይገኙበታል።

በውጭ ከሚኖሩት መካከል ደግሞ የግንቦት7 ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ አቶ ውቤ ሮቤ እና አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ሲገኙበት አቶ መስፍን አማን፣ አቶ ዘለሌ ጸጋስላሴ ፣ ኤልያስ ሞላ፣ ደሳለኝ አራጌ ፣ ኮሎኔል አለበል አመራ፣ ኦባንግ ሜቶ፣ ነአምን ዘለቀ እንዲሁም ከጋዜጠኞች ጋዜጠኛ አበበ በለው፣ አበበ ገላው፣ ፣ ኦባንግ ሜቶ ፣ መስፍን ነጋሽ እና አብይ ተክለማርያም ይገኙበታል።

ፍርድ ቤቱ በጥር ወር ከ1 እስከ 20 ተራቁጥር በተቀመጡት ተከሳሾች ላይ በጸረ -ሽብር  ህጉ አንቀጽ 4 እንዲከላከሉ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።

ተከሳሾች በተከሰሱበት ወንጀል ከሞት እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚደርስ ፍርድ ሊፈረድባቸው ይችላል።

አቶ መለስ ዜናዊ  መንግስታቸው በተከሳሾች ላይ ጠንካራ ማስረጃዎችን  ማሰባሰቡን  በፓርላማ ፊት ቢናገሩም፣ በፍርድ ሂደቱ ወቅት እንደታየው ግን ይህ ነው የሚባል የረባ ማስረጃ ሳይቀርብ ቀርቷል።

በማስረጃነት የቀረቡት አብዛኞቹ ተከሳሾች ለህዝብ ያደረጉዋቸው ንግግሮች ወይም ለጋዜጠኞች የሰጡዋቸው ቃለምልልሶች ናቸው።

ሲፒጄ፣ ሂውማን ራይትስ ወችና  አምነስቲ ኢንተርናሽናል የፍርድ ሂደቱ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው በሚል ውድቅ ማድረጋቸው ይታወቃል። ሴናተር ሊህ፣ ሴናተር ማርክ ቤጊች እና ኤድዋርድ ሮይስ የፍርድ ሂደቱን በማጣጣል እስረኞቹ እንዲፈቱ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑ ዲፕሎማቶችም ግለሰቦቹ በ ሽብርተኝነት ወንጀል የሚያስከስስ መረጃ እንዳልቀረበባቸው በተለያዩ መንገዶች ሲገልጡ ቆይተዋል።

መንግስት በእስረኞቹ ላይ ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ማስረጃዎችን ማቅረብ ሲያቅተው በእስር ቤት ውስጥ በእሰረኞች ላይ ግፍ እንዲፈጸምባቸው አድርጓል። አንዱአለም አራጌ በአንድ እስረኛ እንዲደበደብ፣ ሲደረግ በአቶ ናትናኤል ላይም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ተሞክሮ ነበር።

አቶ አንዱአለም አራጌ ” እየተፈጸመ ያለው ተግባር የተቃውሞ ፖለቲካውን ለማፈን የተወሰደ እርምጃ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ ፍርድ ቤቱ የፈለገውን እርምጃ ሞትም ቢሆን መውሰድ ይችላል።” በማለት መናገራቸው  ይታወሳል።

በነገው እለት የሚሰጠውን የፍርድ ውሳኔ በተመለከተ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር ሀይሉ አርአያ ለኢሳት እንደተናገሩት በእሰረኞቹ ላይ የቀረበውን ማስረጃ ከተመለከትን እስረኞቹ እስካሁንም በእስር ቤት መቆየት አልነበረባቸውም ስለዚህም ፍርድ ቤቱ በነጻ ይለቃቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል። ( 00፡033-1፡45)

በቅንጅት መሪዎች ላይ ጠንካራ ማስረጃዎች ሳይቀርቡ ከፍተኛ ውሳኔ ተወስኖባቸው ነበር፣ የአሁኑ ፍርድ ከዚህ አንጻር እንዴት ይታያል ለተባሉት ዶ/ር ሀይሉ ማስረጃዎች ከታዩ እስረኞቹ ነጻ ይወጣሉ፣ ነገር ግን በእኛ ሁኔታ ፍርድ የሚሰጠው በማስረጃ ሳይሆን በስርአቱ ውሳኔ ነው ብለዋል (2፡06-3፡56)

በእስረኞቹ ላይ የሚወሰነው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን እስረኞችን አግኝታችሁ መንፈሳቸውን እንዲያጠነክሩ ለማድረግ ሞክራችሁዋል ለተባሉት ዶ/ር ሀይሉ፣ እስረኞችን ለመጎብኘት እንደማይችሉ ነገር ግን እነሱ በመንፈስ ጠንካራ መሆናቸውን ገልጠዋል (4፡26-5፡11)

ስሟን መግለጽ ያልፈለገች የአንድ እሰረኛ ባለቤትም ከነገው ውሳኔ ምንም አዲስ ነገር እንደማትጠብቅ ገልጣለች። ፍርዱ ምንም ይሁን ምን እራሱን ዝግጁ ማድረጉዋን ለኢሳት ተናግራለች።

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide