በሻውራ ከተማ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ተከስቷል

መጋቢት ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሰሜን ጎንደር ዞን በአለፋ ጣቁሳ ወረዳ በሻውራ ከተማ የከተማዋ ነዋሪዎች ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ ውሃ በማጣታቸው መቸገራቸውን ለኢሳት ገልጸዋል። አንድ ጀሪካን ውሃ እስከ 20 ብር ለመግዛት

ተገደናል የሚሉት ነዋሪዎች ምክንያቱም ሙስና ነው ይላሉ።

የወረዳው መስተዳደር 300 ሺ ብር የተገዛውን ጄኔረተር 800 ሺ ብር እንደተገዛ አድርጎ ማቅረቡን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ጄኔረተሩ በተሰራ ማግስት መበላሸቱን ገልጸዋል። ጄኔረተሩን ለማሰራት ከፍተኛ ገንዘብ ቢፈስም ሊሳካ ባለመቻሉ ነዋሪው ውሃ በጋሪ እያመላለሱ

ከሚሸጡ ሰዎች ለመግዛት መገደዱን ተናግረዋል። የከተማው ነዋሪ በውሃ ወለድ በሽታ እየተሰቃየ መሆኑንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ የ28 ሆስፒታሎች ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የአማራ ክልል ጤና ቢሮእና ፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ቢገልጹም፤ በኮሶ በር፣ ቻግኒና ዳንግላ ከተሞች ለአገልግሎት ብቁ ናቸው ተብለው የተመረቁት ሆስፒታሎች

ምንም ዓይነት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በ2000ዓ.ም ግንባታውን የጀመረው የኮሶ በር ዞናል ሆስፒታል መጠናቀቅ ካነበረበት ጊዜ  ከአራት አመት በላይ ሲጓተት ከቆየ በኋላ በድንገት ተጠናቋል ተብሎ ከተነገረ በሁዋላ ስራ ይጀምራል ቢባልም፤ ሆስፒታሉ ስራ ሊጀምር ቀርቶ በአግባቡ አለመጽዳቱን የሚናገሩት

ነዋሪዎች ፣ አሁንም አስቸጋሪ የወሊድ እና ከእንጅባራ ጤና ጣቢያ በላይ የሆነ የጤና ችግር ሲኖር ወደ ባህርዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል በመሄድ እንደሚታከሙ ነዋሪዎች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ የሃገር ሽማግሌ አቶ ካሳሁን ከበደ በ2005 ዓ.ም ልጃቸው በመኪና አደጋ ደርሶበት ዞናል ሆስፒታሉ ስራውን መጀመር ባለመቻሉ ወደ ባህርዳር ፈለገ ህይዎት ሪፈራል ሆስፒታል በመሄድ ለልጃቸው ህክምና ፣ለትራንስፖርትና ቀለብ ከ50 ሽህ ብር በላይ

በማውጣት እንዳሳከሙ በዚህም ለወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ገልጸው፤ዛሬ ገና ግንባታው ባለበት የሚሄደውን ሆስፒታል ተጠናቀቀ በማለት ለምርጫ ቅስቀሳ ማዋል አይን ያወጣ ማታለል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ጊዜ ሲደርስ ሁልጊዜም የገዢው መንግስት ህዝብን ለማደናገር የማይሰራቸውን ስራዎች እሰራለሁ በማለት የተለየ ቃል መግባት እንደ ልምድ ማድረጉን የሚናገሩት የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሪት ሰላማዊት  ፣ ባለፈው ሁለት ወር ውስጥ ግንባታውን

ለማጠናቀቅ አለመቻሉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሬዲዮና በጋዜጣ የናገሩት ሁለት ወር ሳይሞላ በድንገት ተጠናቀቀ መባሉ እንዳስደነቃቸው ተናግረው ይህን ለማረጋገጥ ወደ ሆስፒታሉ ሲሄዱ ግን ያገኙት ከአመታት በፊት የነበረውንና ያላለቀ ባዶ ህንጻ መሆኑን

ተናግረዋል፡፡

በባህርዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የልጃቸው ህክምና ሲከታተሉ የነበሩት ወይዘሮ ፅዮን አለሙ ህጻን ልጃቸው በመታመሙ ለህክምና የመጡ መሆኑን ተናግረው “የእንጅባራ ሆስፒታል ተመርቆ  ስራ ባለመጀመሩ ሁሉም የአካባቢው ነዋሪ ለከፍተኛ ህክምና

አሁንም ባህርዳር ነው፡፡”በማለት ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወር በፊት በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ጤና ጥበቃ መምሪያ ዋና ሃላፊ አቶ ውድነህ ገረመ በበኩላቸው “ችግሩ በኮንትራክተሩ እንዝህላልነት የተፈጠረ ነው፡፡እኛም ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ለሚመለከተው አካል ከማሳወቅ

ውጭ ምንም ማድረግ አልቻልንም ፡፡” ብለዋል።

በ90 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተጀመረው የእንጅባራ ዞናል ሆስፒታል በ2007 መጀመሪያ ወራቶች ላይ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አስወጥቷል።

እነዚህን ሰራዎች ከመቸው ተጠናቀው ነው ስራ የጀመረው በማለት የሚጠይቁት የአካባቢው ነዋሪዎች ምርጫ በመጣ ቁጥር  የማይፈጸሙ ቃሎች ህብረተሰቡን እንዳሰለቹ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡

በጥር ወር መጨረሻ ላይ በክልሉ ልዩ ልዩ ዞኖች በመዘዋወር የመሰረት ድንጋይና ያልተጠናቀቁ ሆስፒታሎችን ሲመርቁ የነበሩት የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮነን፣  በእንጅባራ ከተማ ተገኝተው ለህዝቡ ባሰሙት ንግግር በዚህ ታሪካዊ ቀን

ስራው የተጠናቀቀውን ወደ ተግባር ለማስገባት በመታደማችን እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን  ደስ አለን በማለት ስራው ቢጓተትም ዛሬ ወደ መጨረሻ ደረጃ ምዕራፍ ደርሷልና ይህን እንደስኬት እንቁጠረው ፡፡” በማለት ይህ ዘመናዊ ሆስፒታል የህብረተሰቡን የጤና

ንቅናቄ ሊደግፍ ለውጤት መድረሱን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር አፍታም ሳይቆዩ የመጡበትን አላማ በግልጽ ማስቀመጣቸውን የሚያሳይ ንግግር ማድረጋቸው እንዳስደነቃቸው የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣  ወላጆች ልጆቻቸውን በምርጫው ወቅት ምን ማድረግ

እንዳለባቸው በመምከር፤ “ ከፊታችን ያለውን ምርጫ ገዢውን መንግስት እንዲመርጡ የማድረግ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ፡፡” በማለት ቅስቀሳ ማድረጋቸው ይታወሳል

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትውልድ አካባቢያቸው በመገኘት የቻግኒ ሆስፒታልን ቢመርቁም ሆስፒታሉ ከሁለት ወር በላይ ያለምንም አገልግሎት መቆየቱ የአካባቢውን ነዋሪ አሳዝኗል፡፡

የገዢው መንግስት ባለ ስልጣናት በአማራ ክልል በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች በመዘዋወር የማይሰሩ ዩኒቨርስቲዎችን የመሰረት ድንጋይ መጣልና ያልተጠናቀቁ ሆስፒታሎችን መመረቅ የምርጫ ቅስቀሳው አንዱ መንገድ ማድረጋቸው በየአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ትዝብት

ውስጥ እየጣላቸው ነው።