በሻኪሶ የተነሳው ተቃውሞ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2010) ሜድሮክ የወርቅ ማዕድን በሻኪሶ ለተጨማሪ 10 አመታት ኮንትራቱ መታደሱን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ተገለጸ።

በምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞን በበርካታ ከተሞችና የገጠር መንደሮች የተነሳው ተቃውሞ ኮንትራቱ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ነው ተብሏል።

መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሞውን እያሰማ ያለው የጉጂ ህዝብ በአስቸኳይ ሜድሮክ አካባቢውን ለቆ ካልወጣ ርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሜድሮክ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ኮንትራቱ ሊታደስ የነበረው ከሶስት ወራት በፊት ነበር።

በወቅቱ የቄሮዎች ትግል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ኮንትራቱን ማጽደቁ ህዝባዊ ንቅናቄውን የሚያቀጣጥለው መሆኑን የተገነዘበው የህወሃት አገዛዝ ለጊዜው ኮንትራቱ እንዳይጸድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ሰሞኑን እንደተሰማው ግን የሜድሮክ የ10 ዓመት ተጨማሪ ኮንትራት ተራዝሞ ኩባንያው ዳግም ስራውን ሊጀምር ነው።

ይህ መሆኑ የአካባቢውን ህዝብ ለተቃውሞ እንዲወጣ አደረገው።

ትላንት በሻኪሶና በፊንጫ የተጀመረው ተቃውሞ በሁለተኛ ቀኑ በርካታ የምስራቅና የምዕራብ ጉጂ አካባቢዎችን አዳርሷል።

የሜድሮክ የወርቅ ዘረፋን አጥብቀን እናወግዛለን በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ በሁለተኛው ቀኑ ጠንከር ያለ ሲሆን በአብዛኞቹ አካባቢዎች መንገድ በመዝጋት መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ መደረጉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት በሻኪሶ አካባቢ የህዝቡ ኑሮ አስከፊ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በቀላል በሽታዎች የሚሞተው ሰው ቁጥር እየጨመረ ነው። ትምህርት ቤት የለም።

የህክምና ተቋማት በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት የሚገኙ በመሆናቸው ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰቃየ ነው።

የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ከዓመታት በፊት ወደ አካባቢው ለቁፋሮ ሲገባ ለህዝቡ የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶችን እንደሚገነባ ቃል ገብቶ እንደነበር የሚያስታውሱት ነዋሪዎች ቃሉን ሳይጠብቅ ወርቁን ብቻ እየዘረፈ ቆይቷል በማለት በቁጭት ይናገራሉ።

በተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲነሳ በአባዱላ ገመዳና እሳቸውን ተከትለው በኦሮሚያ ክልል መሪነት የተቀመጡ ግለሰቦች በጥቅም ተሳስረው የአካባቢውን ህዝብ ስቃይና መከራ ወደ ጎን ማድረጋቸውንም ነው ነዋሪው የሚገልጸው።

ሰሞኑን በከፍተኛ ቁጣ ተቃውሞ እያሰማ ያለው ህዝብ ሜድሮክ ኩባንያ በአስቸኳይ አከባቢውን ለቆ እንዲወጣ የጠየቀ ሲሆን አለበለዚያ ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

በዛሬው ተቃውሞ በተለይ ከነገሌ ቦረና በ30 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ሀረቀሎ በተሰኘች ከተማ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ ቆሞ መዋሉ ታውቋል።

በምስራቅ ጉጂ ዞን መልካ ሶዳ እና ጎሮዶላ ወረዳዎችም ከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ ተድርጓል።

መንገዶችን በድንጋይና በግዙፍ እንጨቶች በመዝጋት፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ተቃውሞ ሲደረግ መዋሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ጉዳዩን በተመለከተ የመንግስት ምላሽ በይፋ የተገለጸ ባይኖርም የኦሮሚያ ክልል የገጠር አደረጃጀት ቢሮ ሃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በፌስ ቡክ ገጻቸው ሁኔታውን እየተመለከትነው በመሆኑ በትዕግስት ጠብቁ ከሚል ምላሽ በቀር ዝርዝር መረጃ መስጠት አልቻሉም።

በአስቸኳይ ኮንትራቱ ካልተሰረዘ በሚቀጥሉት ቀናት ህዝባዊው ተቃውሞ በሌሎችም አካባቢዎች እንደሚቀጣጠል አስተባባሪዎቹ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።