መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ ባወጣው መግለጫ በደቡብ ኦሮምያ በጉጂ ዞን በሻኪሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ቁጥራቸው 200 የሚጠጋ ተማሪዎች በአዶላ ከተማ መታሰራቸውን ገልጿል።
ብዙዎቹ ወጣቶች ከጸጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት እና ድብደባ መቁሰላቸውን ሊጉ ገልጿል።
የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት እርምጃ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የገለጸው ሊጉ መንግስት እስረኞችን እንዲፈታ፣ ለቆሰሉት አስፈላጊው የህክምና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቋል። አስፈላጊውን ምርምራ በማድረግም ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቅርብ ብሎአል።
በመጨረሻም ብሄሮችን እርስ በርስ ለማጋጨት የሚደረገው ጥረት ሊቆም እንደሚገባው አሳስቧል።
የአካባቢው ባለስልጣናት የከተማውን ህዝብ ሰብስበው በሚያነጋግሩበት ወቅት ህዝቡ ግጭቱን የምታስነሱት እናንተ ናችሁ በሚል የመንግስት ባለስልጣናትን ተጠያቄ አድርጓል።
በግጭቱ አንድ ተማሪ ስትቆስል በርካታ ንብረትም ወድሟል። አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአካባቢው የምክር ቤት አባል ለኢሳት እንደገለጹት ከምርጫ መቅረብ ጋር ተያይዞ በርካታ የጎሳ ግጭቶች ሊነሱ እንደሚችሉ መጠበቅ አለብን ብለዋል። ገዢው ፓርቲ በህዝብ መካከል መከፋፈል እየፈጠረ ሀዝቡ በአንድነት እንዳይቆም እያደረገው መሆኑንና ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ተመሳሳይ ችግሮች በብዛት እንደሚከሰቱ በሻኪሶና አጎራባች ወረዳዎች ያለውን ውጥረት በማንሳት ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢው ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።