በሻኪሶ ተነስቶ ለነበረበው ብጥብጥ ህዝቡ መንግስትን ተጠያቂ እያደረገ ነው

መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአስር ቀናት በፊት በሻኪሶ ከተማ ጎሳን ማእከል አድርጎ በተማሪዎች መካከል በተነሳው ብጥብጥ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ አለበት ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል። የከተማው ባለስልጣናት በግጭቱ ዙሪያ ህዝቡን በማወያየት ላይ ሲሆኑ፣ የከተማው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ለሚነሳው ግጭት የአካባቢው አስተዳዳሪዎች እጅ አለበት ማለታቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለኢሳት ገልጸዋል።

ከተማዋ መረጋጋት ቢታይባትም፣ ተመሳሳይ ችግር ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርሃት መኖሩን ለማወቅ ተችሎአል። መጋቢት5 እና 6 ቀን 2006 ዓም በሁለተኛ ደረጃ እና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች መካከል ጎሳን ማእከል ያደረገ ብጥብጥ ተከስቶ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ የብዙ ነጋዴዎች ህንጻዎችም መስታውቶቻቸው ተሰባብሯል። ሃሙስ መጋቢት 6 በዋለው የከተማው ታላቅ ገበያ ላይ  በተፈጠረ ሁከት በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት መውደሙን ነዋሪዎች ይናገራሉ። አንዲት ነዋሪ በጽኑ ቆስላ ህክምና ተደርጎላት መመለሱዋን እና በግጭቱ የሞተ ሰው አለመኖሩን ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር የዋሉ 12 ሰዎች አለመፈታታቸውም ታውቋል።