መጋቢት 13: 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ስር በምትገኘው የሃርገሌ ከተማ አካባቢ ከሚገኝ ግድብ የተበከለ ውሃን ከተጠቀሙ ነዋሪዎች መካከል በትንሹ ስድስቱ ሞተው በርካታ ለህመም መዳረጋቸውን አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታወቀ።
በክልሉ በመባባስ ላይ ያለው የድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ሰዎች በመሞት ላይ መሆናቸውን የገለጸው የካቶሊክ ዕርዳታ ድርጅት፣ ህይወታቸውን ለመታደግ ሲሉ ከግድቡ የተገኘን ውሃ የሚጠቀሙ ሰዎች ለሞትና ለበሽታ መዳረጋቸውን በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
በተበከለው ውሃ የታመሙ ሰዎች እየተበራከቱ በመሄድ ላይ በመሆኑ የሃርገሌ ከተማ ሆስፒታል ለታማሚዎች በቂ ህክምና ማድረግ አለመቻሉንና ነዋሪዎች ወደ ጎዴ ለመሄድ መገደዳቸውን በስፍራው የሚገኙ የግብረ-ሰናይ ድርጅቱ ቄስ ክርስቶፈር ሃርትሌይ ገልጸዋል።
ይሁንና ለህክምና ወደ ጎዴ ከሚጓዙ ታማሚዎች መካከል በመንገድ የሚሞቱ መኖራቸውን የገለጹት ክርስቶፈር ድርጊቱን በፎቶ አስደግፈው ባሰራጩት ሪፖርት አቅርበዋል።
የካቲት 23 ከሰዓት በኋላ ብቻ ስድስት ሰዎች ለህክምና ወደ ጎዴ ከመጡ በኋላ ህይወታቸው ማለፉንና የተበከለው ውሃ ለበርካታ እንስሳት ሞት ምክንያት መሆኑም ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ መምጣቱን ሲገልፅ ቆይቷል።
በክልሉ በሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት በመኖሩ ምክንያት ውሃ ወለድ በሽታ ሊቀሰቀስ እንደሚችል የእርዳታ ድርጅቶች አሳስበዋል።
በዚሁ የውሃ እጥረት ውስጥ ከሚገኙ የአፍዴር ዞን ነዋሪዎች መካከል የተበከለ የግድብ ውሃን ለመጠቀም የተገደዱ ሰዎች እየደረሰባቸው ያለው ጉዳት በአግባቡ ሊታወቅ አለመቻሉም ተመልክቷል።
የሃርገሌ ከተማ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት አብዲሰላም ሞሃመድ ሆስፒታሉ በተበከለው ውሃ ለህመም እየተዳረጉ ላሉት ሰዎች በቂ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን አስረድተዋል።
በየሆስፒታሉ የሚገኙ ነርሶችም የሰውነት ሙቀት (ትኩሳትን) ለመለካት ቴርሞሜትር እንኳን አለመኖሩን ለግብረ-ሰናይ ድርጅቱ ተወካይ ተናግረዋል።
“የህክምና ዕርዳታን ፈልገው ብዙ ተጉዘው በየሆስፒታሉ የደረሱ ሰዎች ምንም አገልግሎት ሳያገኙ ሲሞቱ መመልከት ልብን የሚሰብር ነገር ነው” ሲሉ ክርስቶፈር የድርቁን አስከፊነት ገልጸዋል።
የሃርገሌ እና የጎዴ ሆስፒታሎች በውሃ መበከሉ ምክንያት ለህመም ተዳርገው የሚገኙ ሰዎችን ለመንከባከብ የመድሃኒት አቅርቦት አመኖሩን ለእርዳታ ድርጅቱ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተጋልጠው ከሚገኙ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት በሶማሌ ክልል የሚገኙ ሲሆን አለም አቀፍ ድጋፍ በወቅቱ ባለመገኘቱ ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት በመባባስ ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።