(ኢሳት ዲሲ–ጥር 27/2011)በሶማሊያ ርዕሰ መዲና ሞቃደሾ ዛሬ አሸባሪዎች የጠመዱት ፈንጂ ፈንድቶ 11 ሰዎች ሲገደሉ 10 ሰዎች ቆሰሉ።
አልጀዚራ እንደዘገበው ሞቃደሾ በሚገኝ በአንድ የገበያ አደራሽ አቅራቢያ ባለ የመኪና ማቆሚያ ውስጥ በተከሰተው ፍንዳታ በፈንጂው ፍንጣሪና በፍርስራሹ 10 ሰዎች ወዲያውኑ መሞታቸው ተረጋግጧል።
ሞቃዲሾ የገበያ አደራሽ ውስጥ በደረሰው በዚህ ፍንዳታ 11 ሰዎች ወዲያውኑ መሞታቸውን የሶማሊያ ፖሊስ መኮንን ሞሃመድ ሃሰን ለሮይተርስ ያረጋገጡ ሲሆን 10 ሰዎች መቁሰላቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ምንም እንኳን ከህንጻው ፍርስራሽ ስር በርካታ አስከሬኖች ሲወጡ ቢታዩም በአጠቃላይ የተመዘገበው የሟች ቁጥር 11 ብቻ እንደሆነም የፖሊስ መኮንኑ ገልጸዋል።
“አሸባሪዎቹ ፈንጂ የጫነውን ተሽከርካሪ በገበያ አደራሽ የመኪና ማቆሚያ ውስጥ በማድረግ ንጹሃንን ፈጅተዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
በሶማሊያ በሚፈጸመው የሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ስሙ በተደጋጋሚ የሚነሳውና በጥቃቱም ሃላፊነቱን ሲወስድ የቆየው አልሽባብ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሃላፊነቱን ስለመውሰዱ የተናገረው ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሶማሊያ በሳሶ ወደብ አስተዳደሪ በታጣቂዎች ተገድለዋል።
ከፊል ራስ ገዝ መብት ባላት ፑንትላንድ ግዛት የሚገኘው ቦሳቦ ወደብ አስተዳዳሪ ፖል አንቶኒ ፎርምሳ የተገደሉት በዛሬው ዕለት መሆኑም ተዘግቧል።
የቦሳሶ ወደብ በዩናይትድ አረብ ኢምሬት ዱባይ ፖርት በተባለው ኩባንያ እንደሚተዳደርም ለማወቅ ተችሏል።