ኦብነግ በይፋ ትጥቅ ሊፈታ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 27/2011)የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር በመጪው ረቡዕ በይፋ ትጥቅ ሊፈታ መሆኑ ተገለጸ።

ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት ግንባሩ ትጥቁን ፈትቶ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን የሚቀጥለበትን አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ፋይል

የግንባሩ ወታደሮች በአምስት ካምፖች እንደሚሰፍሩም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል ለአራት ቀናት ቆይቶ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ትላንትና ማብቃቱን የሶማሌ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።

በጅጅጋ ባለፈው ሳምንት የሃይማኖት ግጭት ተከስቷል በሚል የተሰራጨውን ዘገባም ሃሰት ነው ሲል ቢሮው ለኢሳት ገልጿል።

የትጥቅ ትግሉን ትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ከነገ በስቲያ ረቡዕ በይፋ ትጥቁን የሚፈታበት ስነስርዓት በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

መረጃውን ያረጋገጡት የሶማሌ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዲ አዲል   የክልሉ መንግስትና የኦብነግ አመራሮች በጋራ ያዋቀሩት ኮሚቴ በይፋ ትጥቅ የሚፈታበትን ፕሮግራም እያዘጋጁ ነው ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ገዢ ፓርቲ ሊቀመንበርና በክልሉ ፕሬዝዳንት በአቶ ሙስጠፋ መሀመድ ኡመር ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት መፍታቱንም ሁለቱ አመራሮች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የሶማሌ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዲ አዲል  በቅርቡ በክልሉ ርዕሰ ከተማ ጅጅጋ ተከስቶ የነበረው ግጭት ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነው በሚል የተሰራጨው ዘገባ ሀሰት ነው ሲሉ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ለውጥ ቀልባሾች የፈጠሩት ግርግር እንጂ በሃይማኖት የተጋጨ አካል የለም ብለዋል አቶ አብዲ አዲል።

በባለፈው ሳምንቱ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። ያን ተከትሎም የክልሉ መንግስት የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሎ ነበር።

በተጨማሪም ማንኛውንም ዓይነት የአደባባይ ስብሰባና ትዕይንቶችን ላልተወሰነ ጊዜ የከለከለው የክልሉ መንግስት በለውጥ ቀልባሾች የተቀናበረው ሴራ እስኪመክን ገደቡ እንደማይነሳ አስታውቆም ነበር።

ይሄው ገደብና ክልከላ በትላንትናው ዕለት መነሳቱን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዲ አዲል ለኢሳት ገልጸዋል።

የመጣውን አደጋ መልሰናል፣ ክልሉንም አረጋግተናል የሚሉት ሃላፊው አቶ አብዲ አዲል በአንጻራዊ እይታ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ያለው በሶማሌ ክልል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ ለማጠናከር የተፈጠረውን ችግር በአስቸኳይ በመፍታት በጋር ለመስራት መስማማታቸንም ሃላፊው አቶ አብዲ አዲል ለኢሳት ገልጸዋል።