ጥቅምት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም ስር እንደ አውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም የሴራሊዮን መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን በደቡባዊ ሶማሊያ በግዳጅ ላይ እያለ ሕይወቱን ላጣው ሴራሊዮናዊ ወታደር ፣ የአፍሪካ ሕብረት የሰጠውን የሃምሳ ሽህ ዶላር የደም ካሳ የሴራሊዮን የመከላከያ ሚንስቴር የሆኑት ሌቴናል ጄኔራል ሳሙኤል ኦማር ዊሊያምስ ለሟቹ ባለቤት በክብር ስነስርዓት ገንዘቡን አስረክበዋል።
አገራቸውን በመወከል ግዳጃቸውን ለሚወጡት የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ያላቸውን ክብር እና አድናቆት ገልጸው፣ መንግስታቸው ብሔራዊ ጀግኖቻቸውን መደገፉን እንደማይዘነጋ አሳስበዋል ሲል ሆርስ ሚዲያ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን ወደ ሶማሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ከዘመተው ጦር ውስጥ ምን ያህሉ ሕይወታቸውን እንዳጡና የአካል ጉዳተኛ እንደሆኑ እስካሁን ለሕዝብ ያልተገለጸ ሲሆን፣ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ለፓርላማው ይህን የማሳወቅ ግዴታ የለብንም ማለታቸው የሚታወስ ነው።እስካሁን ድረስ ለጉዳተኛ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ቤተሰቦች የደም ካሳ ይሰጥ አይሰጥ በመንግስት በኩል ለሕዝብ ይፋ የሆነ መረጃ የለም።