ኅዳር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ገዥዎች በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች በማውገዝ ከትናትና ማክሰኞ ረፋድ ላይ የጀመረው የርሃብ አድማ ለሁለተኛ ቀንም ቀጥሏል። ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያን አስቸጋሪው የአየር ንብረት ሁኔታ ሳይበግራቸው ለወገኖቻቸው አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
በስዊድ ፓርላማ ፊትለፊት በመገኘት የስዊዲን መንግስት አንባገነኑን የህወሃት ኢህአዴግ የሚያደርገውን የገንዘብ እና ማንኛውንም ድጋፍ እንዲያቆም ሲሉ ጠይቀዋል። የድማው ተሳታፊ ከሆኑ ግለሰቦች ውስጥ አንዱ አንባገነኑን ስርዓት በማንኛውም አጋጣሚ መታገል እንደሚገባ አሳስበዋል። አስቸጋሪው የዓየር ንብረትን ተቋቁመው ለሁለተኛ ቀን አድማው ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ እንስቶችም በስፍራው ላይ ተገኝተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ችግሮች ጋር ሲነጻጸር እኛ የምንከፍለው መስዋእትነት ምንም ማለት አይደለም ብለዋል። ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን በብሔር እና ሃይማኖት ሳንለያይ ጨቋኙን ስርዓቱን በጋራ መታገል አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዓርበኞች ግንቦት ሰባትን በመወከል በስፍራው የተገኙት አቶ ቢንያም እሸቱ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለውን የጅምላ ግድያ፣ እስራት እና የመብት ጥሰቶችን በማውገዝ አድማውን መቀላለቀላቸውን ገልጸው ሁላችንም ሳንከፋፈል በአንድነት መቆም አለብን ብለዋል።
የርሃብ አድማው አስተባባሪዎች ከርሃብ አድማው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለውን አፈና የሚገልጹ ጽሁፎችን በማሰራጨት ለአገሪቱ ዜጎች እንዲደርሷቸው አድርገዋል። ለቀጣይም ለወገናቸው አጋር መሆናቸውን በጽናት እንደሚቀጥሉበትም ገልጸዋል።