ታህሳስ 07 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአካባቢው ክርስቲያኖች እያለቀሱ ሲናገሩ እንደተደመጡት፤ የቤተ-ክርስቲያኒቱን ጣራ ቀደም ሲል ያፈረሱት የመንግስት ፖሊሶች ነበሩ።
ሰሞኑን ደግሞ በመስተዳድሩ እና በፖሊሶች አስተባባሪነት በቀጠለ ሁለተኛ ዙር የጥቃት ዘመቻ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ሙሉ በሙሉ በእሳት ተቃጥላለች።
ክርስቲያንና ሙስሊም ለዘመናት ተከባብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ተደጋጋሚ ሀይማኖታዊ ግጭቶችን ስታስተናግድ መስተዋሏ ብዙዎችን ማነጋገር ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ግጭቱ፤በህዝብ እየተጠላ የመጣው ገዥው ፓርቲ የሁለቱን ሀይማኖት ተከታዮች በማጋጨት ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት በሚል የተንኮል አስተሳሰብ የፈጠረው ለመሆኑ ብዙዎች በ እርግጠኝነት ይናገራሉ።
ባለፉት ኣመታት በተመሳሳይ በጅማ አብያተ-ክርስቲያናት መቃጠላቸውና ካህናት ጭምር መታረዳቸው ይታወሳል።
“ ይህ ድርጊት ኢትዮጵያዊ አይደለም” ያሉት አንድ ሙስሊም የሆኑ የአካባቢው የአገር ሽማግሌ፤ ነገሩን የጫሩትም፣ያቀጣጠሉትም የመንግስት ፖሊሶች ናቸው። እነሱም በመስተዳድሩ ታዘው ነው” ሲሉ ለኢሳት ወኪል ተናግረዋል።
ጥቃት የደረሰባቸው ክርስቲያኖችም፦” እያስጨረሱን ያሉት መስተዳድሮቹ ናቸው” ሱሉ ተደምጠዋል።
መንግስት ክርስቲያኖችን ከሙስሊሞች ጋር እንዲጫረሱ ከማበረታታት አልፎ ሙስሊሞች እርስ በርሳቸው እንዲጣሉ፣ ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ እንዲከፋፈሉ ያደርጋል የሚል ክስ በተደጋጋሚ ይቀርብለታል።
በቅርቡ አህባሽ የተባለ የእስልምና ሀይማኖት አስተምሮ ለማስፋፋት በሚል በሙስሊሞች መካከል ያለውን ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶታል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ መካከል ጣልቃ በመግባትም ቤተክርስቲያኑ እንድትከፋፈል አድርጓል ተብሎ ወቀሳ እየቀረበበት ነው።
በስልጤ የተፈጠረውን የሀይማኖት ግጭት በማስመልከት አንድ ከአድማስ ለአድማስ የተባለ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ” መለስ ከስልጣን ለመቆየት የሚጠቀምበት ፍልስፍና (እንደሱ አባባል ዲሞክራሲ) ህዝብን በዘር እና በሃይማኖት በጎሳ እየከፋፈሉ ህዝቦች አንድነት እንዲያጡ ማድረግ እና ሰዎች በመንግስት ለይ ከማመጽ ይልቅ እርስበርስ እዲጠላሉ ማድረግ ነዉ። ይሄ ያደባባይ ሚስጥር ነዉ ። መለስ አንድ ቀን ለህዝቡ እግዚያብሄር ማስተዋልን ሲሰጥ ዋ! አንተን አያርገኝ” ብለዋል።