(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 26/2011) በሲዳማ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች መምህራን አድማ መቱ።
መምህራኑ አድማውን የመቱት ለህዳሴው ግድብ የሚቆረጠው ደሞዛቸው እንዲቆም በመጠየቅ ነው።
እስካሁንም ሲቆረጥ የነበረው እንዲመለስላቸው መምህራኑ አድማ በመምታት ጠይቀዋል።
የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ እስኪሰጣቸውም ወደ ስራ ገበታቸው እንደማይመለሱ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ መምህራን ለህዳሴው ግድብ ከደሞዛቸው የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲቆም በመጠየቅ ከአንድ ሳምንት በላይ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ቱኒዚያን መነሻ አድርጎ የተቀጣጠለውን የአረቡን ዓለም አብዮት ተከትሎ በድንገት ይፋ የተደረገው የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በእጥፍ አልፎም መጠናቀቅ አልቻለም።
የሂደቱን ግማሽ መጓዝ አቅቶት እየተንፏቀቀ ይገኛል።
በሀገር ሀብት፣ በሀገር ልጅ ይገነባል ተብሎ በ2003 ዓም እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር የተጀመረውና 80ቢሊየን ብር ይፈጃል የተባለው የግድቡ ፕሮጀክት በሜቴክና በሌሎች የህወሃት ኩባንያዎች ግልጽ ዘረፋ መፈጸሙን በተመለከተ ኢሳትና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በየጊዜው መረጃዎችን ሲያወጡ ቆይተዋል።
የዓለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ አበዳሪ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የፕሮጀክቱ አዋጭነት ላይ ጥያቄ በማንሳታቸውና ከኢትዮጵያ አቅም አንጻር የተጋነነ መሆኑን በመግለጽ ብድር የነፈጉት ፕሮጀክት ከኢትዮጵያውያን ኪስ እየተወሰደ እንዲሰራ መወሰኑ ብዙዎችን ስጋት ውስጥ ከቶ ነበር።
ሰራተኛው፣ ነጋዴው፣ መምህሩ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አስገዳጅ በሆነ መልኩ በተዘረጋ የቦንድ ግዢ ከደሞዙ እየተቆረጠ ለአባይ ግድብ እንዲውል መደረጉ በጊዜው ሀገራዊ ፋይዳውን በማየት ድጋፍ ተሰጥቶት እንደነበርም አይዘነጋም።
ሆኖም ፕሮጀክቱ ከታቀደለት ጊዜ በእጅጉን ወደ ኋላ መቅረቱ ድጋፍ የሰጡትን ወገኖች ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።
በተለይም ለህወሃት የንግድ ተቋማት ግልጽ ዘረፋ እየተጋለጠ ሲመጣ ከየቦታው የህዝብ ተቃውሞ መሰማት ጀምሯል።
ለአባይ ግድብ የሚቆረጥብን ገንዘብ ይቁም የሚለው የሲዳማ ዞን መምህራን ጥያቄ በእርግጥ የአሁን አዲስ አይደለም።
ከዚህ ቀደምም የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በየአካባቢው በሚዘዋወርበት ወቅት ተመሳሳይ ተቃውሞ በሲዳማ ዞን መምህራን ዘንድ ተነስቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ሰሞኑን በሲዳማ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ መምህራን ጥያቄውን በማንሳት ብቻ አልቆሙም።
የስራ ማቆም አድማ በመምታት ከደሞዛቸው ለግድቡ እየተቆረጠ ያለው ገንዘብ እንዲቆም ጠይቀዋል።
በአለታወንዶ፣ጩኮ፣ ሀገረሰላም፣ ቦርቻ፣ ዳራና በሌሎች የሲዳማ ዞን አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚሰሩ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ያሉ መምህራን ሰሞኑን የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት እየተዘረፈ ላለ የግድቡ ፕሮጀክት ደሞዛችን አይቆረጥም በሚል እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መምህራኑ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በአድማው የቆዩ ሲሆን ጥያቄአቸው ምላሽ እስከሚያገኝ እንደሚቀጥሉ ነው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ መምህር ለኢሳት የገለጹት።
መምህራኑ እስከአሁንም የተቆረጠባቸው ገንዘብ እንዲመለስላቸውም ጠይቀዋል።
ሲመለስም በቦንድ ሳይሆን በገንዘብ እንዲሆን ነው ጥያቄ ያቀረቡት።
የሲዳማ ዞን የአባይ ቦንድን የሚያስተባብረው ጽሕፈት ቤት እስከአሁን ምላሽ አልሰጠም።
በይርጋለም ከተማ የሚገኙ መምህራን ለሁለት ዓመት እንዲቆረጥ የተስማሙትን ደሞዛቸውን አንድ ዓመት ከተቆረጠባቸው በኋላ ማስቆማቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከሁለት ሳምንት በፊትም በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ መምህራን ለህዳሴው ግድብ ያዋጣነዉ ገንዘብ እና ቦንድ የት ደረሰ በሚል ላነሱት ጥያቄ ምላሽ በማጣታቸው የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ይታወሳል።