ኢሳት (ህዳር 21 ፥ 2009)
ሰሞኑን ከሸቀጣ-ሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር በተገናኘ በሱዳን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ተጠናክሮ ቀጠለ።
በተማሪዎች ተጀምሮ የነበረው ይኸው ተቃውሞ ረቡዕ የህግ ባለሙያዎችን በማቀፍ በሱዳን መንግስት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ትዕይንት በመዲናይቱ ካርቱም ረቡዕ ለሁለተኛ ጊዜ ሲካሄድ መዋሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከቀናት በፊት የሃገሪቱ ተማሪዎች መንግስት በነዳጅ ምርት ላይ ሲያደርግ የነበረው ድጎማ መነሳት መሰረታዊ የሸቀጣሸቀጦች ዋጋ መናር ምክንያት ሆኗል በማለት በካርቱም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል።
ይሁንና ህዝባዊ ተቃውሞው መልኩን በመቀየር በሰብዓዊ መብት መከበር ላይ በአዲስ መልክ በመስፋፋት ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በመሰራጨት ላይ መሆኑን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።
የሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር ከ20 አመት በፊት ለስልጣን ከበቁ በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ ነው የተባለ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተካሄደባቸው እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ረቡዕ በካርቱም አደባባይ የወጡ የህግ አካላትን ለመበተን የጸጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጢስ ቢጠቀሙም በርካታ ሱዳናዊያን በአልበሽር መንግስት አገዛዝ ላይ የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ መዋላቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።
የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ህዝባዊ ተቃውሞን ለመቆጣጠር የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ለእስር ቢዳርጉም ተቃውሞ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።
በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ውጥረት የነገሰ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ህዝባዊ ተቃውሞ በሱዳን ሁለተኛ ከተማ በሆነችው ኦማዱርማን መዛመቱ ታውቋል።
በተለያዩ ከተሞች አደባባይ የወጡ ሱዳናዊያን የአልበሽር መንግስት የዴሞክራዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ እንዲመለስ አሳስበዋል።
የፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር በሃገሪቱ የዳርፉር ግዛት ተፈጽሟል ከተባለ የጦር ወንጀል ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት ተብለው በአለም አቀፉ የጦር ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ይታወሳል።
በአፍሪካ ለረጅም አመታት በስልጣን ከቆዩ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አልበሽር ፓርቲያቸው በስልጣን እንዲቆዩ ለማደረግ አፈናን እየፈጸሙ እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ፕሬዚደንቱ ከአንድ አመት በኋላ በሃገሪቱ ከሚካሄደብ ብሄራዊ ምርጫ እንደማይሳተፉ በቅርቡ ቢገልጹም፣ ገዢው የሱዳን ፓርቲ በስልጣን ለመቆየትና አልበሽርን ዳግም ፕሬዚደንት ለማደረግ እቀድ መደደፉን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
ይህንንም ተከትሎ የሱዳን የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድርጊቱን በመቃወም ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።