የውጭ ባለሃብቶች ከሃገር ውስጥ ባለሃብቶች እኩል ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች የብድር ፖሊሲ እንዲከለስ ትዕዛዝ ተላለፈ

ኢሳት (ህዳር 21 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ መቀነስን ተከትሎ መንግስት የውጭ ባለሃብቶች ከሃገር ውስጥ ባለሃብቶች እኩል ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች የብድር ፖሊስ በድጋሚ እንዲከለስ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ተገለጸ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቅርቡ ያልስተላለፈውን ውሳኔ በመሻር በተለይ በአበባና ፍራፍሬ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከሃገር ውስጥ ባለሃብቶች እኩል ብድር እንዲያገኙ እንዲደረግ ውሳኔን መሰጠቱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወራት በፊት ተግባራዊ ባደረገው አዲስ መመሪያ በዘርፉ የተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ለመሰማራት ወደ ሃገሪቱ ሲመጡ 50 በመቶ የፕሮጄክት ወጪን ራሳቸው እንዲሸፍኑ መወሰኑ ይታወሳል።

ይሁንና መንግስት በአዲስ መልክ በስራ ላይ ያዋለው መመሪያ በውጭ ባለሃብቶች ከኢንቨስትመንት ስራ ራሳቸውን እንዲያርቁ ማድረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።

በዘርፉ ታይቷል የተባለውን የኢንቨስመንት መቀዝቀስ ተከትሎም በአበባና ፍራፍሬ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች ለስራቸው 25 በመቶ የሚሸፍነውን ካፒታል በመያዝ 75 በመቶ ከመንግስት ብድር እንዲመቻችላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ልዩ ጥቅማጥቅም ሲደረግላቸው የቆየው የውጭ ኩባንያዎች ለህገሪቱ ማስገኘት የነበረባቸውን የውጭ ምንዛሪ አላስገኙም በማለት በብድር ዘርፍ ሲቀርብ የነበረው ልዩ ዕድል እንዲቀንስ መወሰኑ ይታወሳል።

ባለፈው በጀት አመት ከውጭ ንግድ ገቢ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ለማግኘት እቅድ ቢያዝም ከዘርፉ ግማሽ ያህሉ ብቻ ሊገኝ መቻሉን የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ሃገሪቱ ያጋጠማትን የንግድ ገቢ መቀነስ ተከትሎም የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በከፍተኛ መጠን የቀነሰ ሲሆን፣ ድርጊቱ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አደጋ መጋረጡን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የአለም ባንክ በበኩሉ ኢትዮጵያ ባጋጠማት የኢኮኖሚ መዋዠቅና የንግድ ገቢ መቀነስ ምክንያት በሁለት አሃዝ ያድጋል ተብሎ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት በስድስት በመቶ ብቻ ሊያድግ እንደሚችል ይፋ አድርጓል።

የመንግስት ባለስልጣናት የኢኮኖሚውን መዋዠቅና የንግድ ገቢ መቀነስ ምክንያት በሁለት አሃዝ ያድጋል ተብሎ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት በስድስት በመቶ ብቻ ሊያድግ እንደሚችል ይፋ አድርጓል።

የመንግስት ባለስልጣናት ኢኮኖሚውን 12 በመቶ ያድጋል ሲሉ በመጠን የተራራቀን ትንበያ አስቀምጠዋል።