(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 19/2011) በሱዳን የተቀሰቀሰውና ካሳምንት በላይ የቀጠለውን ተቃውሞ ጋዜጠኞችም መቀላቀላቸው ተሰማ።
የሱዳን መንግስት የተቃውሞ እንቅስቃሴውን እንዳንዘግብ ጫና እያደረገብን ነው ያሉ ጋዜጠኞች ከሃሙስ ጀምሮ አድማ ሲመቱ አንዳንድ የውጭ ሃገር ዘጋቢዎች ከሃገር እንዲወጡ ታዘዋል።
የሱዳን መንግስት ዓመጹን የእስራኤልን መንግስት እጅ አለበት በማለት በይፋ መግለጫ ሰቷል።
የሱዳን ጋዜጠኞት ኔትወርክ (SJN) ትናንት ሃሙስ እንዳስታወቀው መንግስት የጋዜጠኞችን ስራ ለመቆጣጠር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም የሶስት ቀናት የጋዜጠኞች አድማ ተጠርቷል።
“ተቃውሞው ከተጀመረበት ግዜ ጀምሮ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ወከባና እንግልት እጅግ አሳስቦናል” በማለት በመግለጫው የጠቀሰው የሱዳን የጋዜጠኞች ኔትወርክ ዘጠኝ የሚሆኑ አባላቱ ተቃውሞውን ስለዘገቡ ብቻ እስራትና ድብደባን ጨምሮ መንገላታት እንደተፈጸመባቸው አስታውቋል።
ይህም በሶስት ቀናት አድማ ለማድረግ ምክንያት እንደሆነውም አመልክቷል።
የውጭ ሃገር ጋዜጠኞች ስራቸውን እንዲያቆሙ መደረጋቸውን፣ የተወሰኑት ደግሞ ከሱዳንም ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን የሱዳን የጋዜጠኞች ኔትወርክ አስታውቋል።
የሱዳን እለታዊ ጋዜጣ አልጣየር ዋና አዘጋጅ ካሊድ ፋታይ ለቱርክ ዜና አገልግሎት አናዳሉ በሰጠው ቃለ ምልልስ በካርቱም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመዘገብ በተገኘበት በፖሊስ መደብደቡን ገልጿል።
በዳቦና በነዳጅ ላይ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ ሱዳን ውስጥ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ፕሬዝዳንት አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ ወደ መጠየቅ ተሸጋግሯል።
የህክምና ባለሙያዎችም ተቃውሞውን መቀላቀላቸውን ትላንት መዘገባችን ይታወሳል።
የሱዳን መንግስት ተቃውሞውን ከእስራኤል መንግስት ተልዕኮ የተቀበሉ ሰዎች እያቀጣጠሉት ነው በማለት 18 ተማሪዎችን ተጠያቂ ናቸው ሲል በቴሌቪዥን አቅርቧል።
በሌላም በኩል ሃገሪቱ ውስጥ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘ የበጀት ማስተካከያ ያለውን ርምጃ መውሰድ ጀምሯል።
የመንግስት በጀትን ለመቀነስ በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግስት ባለስልጣናት የመንግስት ተሽካርካሪ እንዲያስረክቡ ታዘዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 30/1989 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት ጄኔራል ኦማር አልበሽር የኢፍታችን ሰኔ ወር ስልጣን ከያዙ 30 አመት ይሞላቸዋል።