በሰሜን ጎንደር አንድ የኮማንድፖስት አባል ሁለት ወጣቶችንና አንድ ፖሊስ ሲገድል  የወልቃይት ተወላጆችም እየታደኑ ነው ።

ኅዳር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- አገሪቱን እየመራ ያለው ወታደራዊ እዝ በእንግሊዝኛው ኮማንድ ፖስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጽማቸው ግድያዎችና አፈናዎች እየጨመሩ በመምጣት ላይ ናቸው። በሰሜን ጎንደር በወገራ ወረዳ በዳባት ከተማ ከአካባቢው አርሶአደሮች ተውጣጥቶ ጉጅሌ የሚል መጠሪያ የተሰጠው የኮማንድ ፖስት አባል የሆነው ንጋት ምስጋናው ሁለት የወገራ ደሲያ አካባቢ ተወላጆችን ከእስር ቤት በማውጣት በጥይት ደብድቦ የገደላቸው ሲሆን፣ የአካባቢው ተወላጅ የሆነው ፖሊስ ስጦታው አቡሃይ “ ጉጅሌውን” ሲቃወመው፣ ጉጅሌውም “ የፈለኩትን እርምጃ እንድወስድ መብት ተሰጥቶኛል” በማለት ፖሊሱን በጥይት መቶታል። ፖሊስ ስጦታው ከወደቀበት ቦታ ላይ ሆኖ ጉጅሌ ምስጋናውን መልሶ በጥይት መትቶታል። ጉጅሌው ጀርባው አካባቢው ክፉኛ ተመትቶ ጎንደር ሆስፒታል በመታከም ላይ ሲሆን፣ ፖሊስ ስጦታው ግን ህይወቱ አልፏል።

የሁለቱ ወጣቶች የቀብር ስነስርዓታቸው በወገራ ደሲያ ሲፈጸም፣ የፖሊስ ምስጋናው ደግሞ በደንከር ልደታ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል። ወጣቶቹ የተያዙት በወገራ ወረዳ መንገድ ዘግታችሁ ተቃውሞ አሰምታችሁዋል በሚል ነበር። ህወሃት የአካባቢው ተወላጆች ታጣቂዎችን የኮማንድ ፖስት አባል የሆነና ያልሆነ በማለት ከፋፍሎ እንዲጋለዱ እያደረገቻው መሆኑን የአካባቢው ተወላጅ ታጣቂዎች ሊያውቁት ይገባል በማለት ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የሰሜን ጎንደርን የወታደራዊ እዝ በበላይነት እየመራ በህዝብ ላይ እልቂትና ስርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር የሚያደርገው የሁመራ ዋና አስተዳዳሪ የነበረውና በአሁኑ ሰአት ወደ ጎንደር ከተማ የተዛወረው አቶ ኢሳያስ የተባለው ግለሰብ ነው። ግለሰቡ የወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሶ የኮሎኔልነት ማእረግ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት ምንጮች፣ በ1997 ዓም የጉለሌ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም አቶ መለስ ዜናዊ በ1997 ባቋቋሙት ወታደራዊ መምሪያ አባል ሆኖ የሰራና የበርካታ ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈ የህወሃት አባል ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዚህ ግለሰብ አመራር በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች እየታደኑ በመያዝ ላይ ናቸው። አቶ ዘውዱ የተባሉ የወልቃይት ተወላጅ ከትግራይ ክልል ማደኛ ወረቀት ወጥቶባቸዋል በሚል ተይዘው ታስረዋል። ሌሎች የወልቃይት ተወላጆችም ከትግራይ ክልል ማደኛ ወጥቶባቸው እየተፈለጉ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በህወሃት አባላት የኮማንድ ፖስት የሚመራው የአማራ ክልል ከትግራይ ክልል ማደኛ ወጥቶባቸው ለሚፈለጉ ሰዎች ምንም አይነት ከለላ ባለመስጠት ተይዘው እንዲወሰዱ እያደረገ ነው።

በሌላ በኩል የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ም/ል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሲሳይ አያና ህዳር 2 ቀን 2009 ዓም በኮማንድ ፖስት አባላት ይፈለጋሉ በሚል ታፍነው ከተወሰዱ በሁዋላ ዛሬ ያሉበት ቦታ መታወቁን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ አቶ ሲሳይ ቀበሌ 18 በሚገኛው 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ የገለጹት ምንጮች፣ እስካሁን ድረስ ክስ አልቀረበባቸውም።