በርካታ ጥራት አልባ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በነዋሪዎች ህይወት ላይ አደጋ ደቅነዋል ተባለ

ሰኔ ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያሉ በርካታ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ከጊዜ በሁዋላ በተገልጋዮች ህይወት ላይ አደጋ መደቀናቸውን የግንባታ ባለሙያዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት አብዛኞቹ ቤቶች የሚሰሩት አስቀድሞ ጥልቅ የሆነ የአፈር ምርመራ ሳይደረግባቸው በመሆኑ ከጊዜ በሁዋላ ጉዳት ማስከተላቸው አይቀሬ ነው። መሃንዲሶች እንደሚሉት አብዛኛውን ጊዜ የኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚገነቡት ሜዳ እንደተገኘ እንጅ በትክክል የአፈር ምርመራ ተካሂዶባቸው ባለመሆኑ፣ ከጊዜ በሁዋላ የመንሸራተትና የመስመጥ አደጋ ያጋጥማቸዋል። በስራ ላይ ያሉ አንዳንድ ጅምር ኮንዶሚኒየም ቤቶች እየሰመጡ መምጣታቸውን የሚናገሩት መሃንዲሶች፣ መንግስት ችግሩን ቢያውቀውም እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አይደለም። ከቪዲዮዎቹ ለማየት እንደሚቻለው በ አንዳንድ የኮንዶሚኒየም ብሎኮች ገና ከመጀመራቸው በመሰረቱና በተሸካሚው ቢም መካካል ያለው ክፍተት እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው።

በሚቀጥሉት 10 አመታት ቤቶቹ ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ከዚህ በሁዋላ የሚገነቡት ግንባታዎች ከመጀመራቸው በፊት አስቀድሞ የአፈር ምርመራ ጥናት ሊደረግላቸው እንደሚገባ ይመክራሉ።