በረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከፍተኛ ሙስና መፈጸሙን የውስጥ ምንጮች ገለጹ

በረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከፍተኛ ሙስና መፈጸሙን የውስጥ ምንጮች ገለጹ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ/ም ) ከ120 ሚሊዮን ዶላር ወይም አሁን ባለው ምንዛሬ ከ3 ቢሊዮን ብር ያላነሰ በጀት ተመድቦለት የተሰራው የአዲስ አበባ ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከውል ስምምነት ጀምሮ ሙስና የተፈጸመበት እንደሆነና ለዚህም ዋናው ተጠያቂ በወቅቱ የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ቦርድ ዳይሬክተር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

በዶ/ር ደብረጺዮን ትዕዛዝ ስራው ከ5 አመት በፊት ፕሮጀክቱ ኬምብሪጅ እንዱስትሪስ ሊሚትድ ለተባለ ኩባንያ ያለግልጽ ጫረታ መሰጠቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ መብራት ሃይል ያለ ጨረታ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለውጭ ኩባንያዎች የሚሰጠው ኩባንያዎቹ የውጭ አገር ገንዘብ ይዘው መመጣታቸው ሲረጋገጥ ቢሆንም፣ ኬምብሪጅ ኡንድስትሪስ ኩባንያ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሚሸፈን ወጪ ያለጨረታ ስራውን እንዲሰራ የተሰጠው በመሆኑ የተለዬ ያደርገዋል።
ኬምብሪጅ ኩባንያ የውጭ አገር ኩባንያ አለመሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ ኩባንያው በብሪቲሽ ቨርጂን አይላንድስ እንደተመዘገበ በውል ስምምነቱ ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ቢሆንም፣ የኩባንያው የአክሲዮን ባለቤቶች የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ብሪቲሽ ቨርጂንያ አይላንድስ የተለያዩ ኩባንያዎች ባለቤቶች ታክስ እንዳይከፍሉ ሃብታቸውን ህገወጥ በሆነ ሁኔታ የሚደብቁበት ቦታ መሆኑን ፋይናንሻል ታይምስ ካፒታል ኢኮኖሚክስን ጠቅሶ ዘግቧል። ኢሳት ኬምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ኩባንያ በውል ስምምነቱ ላይ በተጠቀሰው አድራሻ መሰረት በጎግል ፍለጋ ቢያደርግም፣ ስለኩባንያው የሚገልጽ ምንም ነገር ማግኘት አልቻለም። ኬምብሪጅ ከረጲ ጋር በተያያዘ ከከፈተው ዌብሳይት በስተቀር ፣ ስለድርጅቱ የሁዋላ ታሪክም ሆነ በአለማቀፍ ደረጃ ስለሰራቸው ስራዎች የሚያመለክት ምንም መረጃ የለም።
የኩባንያው ዋና ዳይሬክተር ተብለው የተጠቀሱትን ሮበርትስ ብሩክን ማንነት ለማወቅ በጎግል ፍለጋ ብናካሂድም ግለሰቡ፣ ከፋይናስ ጋር በተያያዘ ስራ እንደሚሰሩ ከመገለጹ ውጭ ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም። ስለሳቸው የወጣ አንድ መለስተኛ መረጃ እንደሚያሳየው ግለሰቡ ማኔጅንግ ዳይሬክተር እንዳልሆኑ፣ ከኬምብሪጅ ኡንዲስትሪያል ግሩፕ ጋር አጋር ማኔጀር ( ማኔጂንግ ፓርትነር ) መሆናቸውን ብቻ ተጠቅሷል።
ምንጮች እንደሚሉት ኬምብሪጅ ኢንዱስትሪስ የተባለው ድርጅት በሃይል ማመንጨት ስራ ምንም ልምድ የሌለው መሆኑን በማወቅ የቀድሞው የመብራት ሃይል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምህረት ደበበ ኮንትራቱን ለማቋረጥ ሙከራ አድርገው እንደነበር፣ ይሁን እንጅ ዶ/ር ደብረጺዮን “ የኩባንያውን ማንነት ለማወቅ ለምን ትፈልጋለህ፣ ምን አገባህ” ብለው እንደጮሁበት፣ አቶ ምህረት ያዘጋጁትን የጨረታ ሰነድም ፊቱ ላይ እንደወረወሩበት እና አቶ ምህረትም ተገደው ኮንትራቱን እንዲፈርሙ ተደርገዋል።
ኬምብሪጅ የመብራት ሃይል ጋር እንደተፈራረመ ወዲያውኑ ስራውን ሲ ኤን ኢ ኢ ሲ ለተባለ የቻይና ኩባንያ በመለስተኛ ተቋራጭነት ሰጥቶ ማሰራቱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ኬምብሪጅ ምንም ስራ ሳይሰራ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ጽ/ቤት ሳይከፍት ገንዘብ መውሰዱን ይገልጻሉ።
ኩባንያው በስምምነቱ መሰረት 50 ሜጋ ዋት ሃይል እንደሚያመነጭ ቢጠበቅም፣ ውሉን በመተው 25 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዲዛይኑን መቀየሩን፣ ዶ/ር ደብረጺዮንም የመብራት ሃይል ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትን ወ/ሮ አዜብ አስናቀን አስገድደው አዲሱን ዲዛይን እንዲቀበሉና ክፍያ እንዲፈጽሙ ማደረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ኬምብሪጅ በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት ማሟላት ያለበትን ነገር ሳያሟላ ፕሮጀክቱን ለማስረከብ ፍላጎት ያለው ቢሆንም፣ የመብራት ሃይል ሰራተኞች ፕሮጀክቱን ለመረከብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ነበር። ወ/ሮ አዜብና የፕሮግራም ዳይሬክተሩ አቶ ፍሰሃ ገብረመስቀል፣ የሰራተኛውን ውትወታ ባለመስማት ፣ ስራው ሳይጠናቀቅ የምረቃ ዝግጅት እንዲዘጋጅ ያደረጉ ሲሆን ፣ እነዚህ ሰዎች የአመራርና የጥገና ስራውን ለኬምብሪጅ ኩብንያ እንዲሰጥ ሲያሳስቡ ቆይተዋለ:፡
ዶ/ር አብይ በጉዳዩ ላይ በፍጥነት ገብተው የተፈጸመውን ሙስና እንዲጣራ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት ሰዎች አሳስበዋል።
ፕሮጀክቱ በቅርቡ በፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ተመርቆ መከፈቱ ይታወቃል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመብራት ሃይል ባለስልጣናትን፣ የኬምብሪጅ ሃላፊዎችን፣ አቶ ምህረት ደበበንና ዶ/ር ደብረጺዮንን ጨምሮ የመንግስት ባለስልጣናት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በጉዳዩ ዙሪያ ስማቸው የተጠቀሱት ግለሰቦች መልስ የሚሰጡን ከሆነ በሚቀጥለው ዘገባ ይዘን እንቀርባለን።