በራያ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እንዲቆም የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተደረገ።

በራያ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እንዲቆም የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተደረገ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ/ም ) የትግራይ ክልል በልዩ ጦሩና በሚሊሺያው አማካኝነት የሚፈጽመውን የመብት ጥሰት እንዲያቆም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
መነሻቸውን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ያደረጉት ሰልፈኞቹ ፍትህ ለራያ ሕዝብ፣ ማንነታችን ይከበር፣ የትግራይ ልዩ ኃይል የሚፈጽመውን ጭፍጨፋ ያቁም፤ የሚሉና የተለያዩ መፈክሮችን አሰምተዋል። በሕዝብ ቀረጥ የሚተዳደረው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኢቲቪ ለራያ ሕዝብ የመብት ጥሰት የሚዲያ ሽፋን አልሰጠም፤ የህዝቡን ሰቆቃ መላው ኢትዮጵያዊ እንዲያውቅልን ይደረግ፤ ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ሰልፈኞቹ በመቀጠል ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በማምራት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። የማንነት ጥያቄያችን ይረጋገጥልን፤ መንግስት የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልን በማስወጣት የፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊትን በማስገባት ሕዝቡን በአፋጣኝ ከጥቃት እንዲታደግ ብለዋል። የፌደሬሽን ምክር ቤት በበኩሉ ጥያቄያቸውን በቅደም ተከተሉ ከትግራይ ክልል ጀምሮ በማቅረብ ሕጋዊ መንገዱን ተከትለው እንዲሰሩ ሲሉ ኃላፊው መግለጻቸውን የራያ ሕዝብ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አገዘው ህዳሩ ገልጸዋል።
ባለፉት 27 ዓመታት የቀጠለው የራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ሰሞኑን ተባብሶ መቀጠሉንም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል። በተይም በአላማጣ፣ ዋጃ፣ ከተሞች የትግራይ ልዩ ኃይል፣ ልዩ ኮማንዶ፣ የክልሉ ሚኒሻን ጨምሮ በቅርቡ ለ15 ቀናት ስልጠና የተሰጣቸው ምልምል ሚሊሻዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ማንነታችን ህጋዊ እውቅና ይሰጠው ያሉ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ኢሰብዓዊ ጥቃት እየፈጸሙ ነው። በራያ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግድያና መፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም መንግስት አፋጣኝ እልባት እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።
በቀድሞው መንግስታት የራያ ሕዝብ በወሎ ጠቅላይ ግዛት እና በወሎ ክፍለሃገር ውስጥ ሲተዳደር የነበረ ሲሆን ህወሃት/ኢህአዴግ መንበረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ካለ ሕዝቡ ፍቃድ ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለል መደረጉ ይታወሳል።