ታህሳስ ፲፰ ( አስራ ስምንት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አልሸባብ እንዳጠመደው በሚገመተው ፈንጅ ከሞቱት መካከል 6ቱ ወታደሮች ናቸው ተብሎአል። አንድ የሞቃዲሹ ፖሊስ ባለስልጣን ግን የሞቱት ወታደሮች ቁጥር 3 ናቸው ይላሉ።
ወታደሮች ወርሀዊ ደሞዛቸውን ተቀብለው በምግብ ቤቱ ውስጥ እንደተገኙ ፍንዳታው መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል። የምግብ ቤቱን ባለቤት ጨምሮ 5 ሲቪሎች የተገደሉ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ፍንዳታውን አደረስኩ የሚል ወገን መግለጫ አልሰጠም።
አልሸባብ ከሞቃዲሹ ከወጣ ጀምሮ በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም፣ አልፎ አልፎ በሚደረጉ ጥቃቶች የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ ነው።
የኢትዮጵያ ጦር ካለፉት 2 አመታት ጀምሮ በሶማሊያ ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ጦር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር እንዲታቀፍ የኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ፈቃደኝነት በመጥፋቱ እስካሁን አልተሳካለትም።