ሐምሌ ፲(አስር)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የምስራው አፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ሊግ የተሰኘው ድርጅት ለኢሳት በላከው መረጃ ከ10 ቀናት በፊት ልዩ ሚሊሺያ እየተባሉ የሚጠሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት በ ኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በቀምቢ ወረዳ በጋራ ወሎ ቀበሌ በነዋሪዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የ38 አመቱ ጎልማሳ ኢብራሂም ሄኖ፣ የ26 እና 27 አመት ወጣቶች ሙሀመድ ሙሳና ሙሀመድ የሱፍ ሲገደሉ፣ የ25 አመቱ ኑረዲን እስማኤል እና የ27 አመቱ አሊ ሙሀመድ ክፉኛ ቆስለው ሀረር ውስጥ በሚገኘው ህይወት ፋና ሆስፒታል ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ አባላት በሶማሊ እና በኦሮምያ ወሰኖች መካከል የሚታየውን ግጭት ሰበብ አድርገው የኦሮሞ ተወላጆች አካባቢውን እንዲለቁ ማስገደዳቸውን ሊጉ ገልጿል። በአካባቢው ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች አካባቢውን ለቀው በመውጣታቸው ሟቾቹ ቀባሪ አጥተው በጅብ መበላታቸውን የሰብአዊ መብት ድርጅቱ አስታውቋል።
ካለፉት 8 ወራት ጀምሮ በሚካሄደው ከድንበር ነዋሪዎችን በማስወጣቱ እርምጃ ብዙዎች ንብረታቸው ተዘርፎአል።
ለጠቅላይ ሚ/ር ሀይለማርያም እና ለሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተላከው በዚህ መግለጫ፣ መንግስትና የሚመለከታቸው ወገኖች አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቋል።
የኦጋዴን ተወላጆች በአካባቢው የመሬት ጥያቄ እንደሌላቸው የገለጸው ድርጅቱ፣ እርምጃው በፌደራል ፖሊስ አባላት የሚካሄድ ነው ብሎአል።
መንግስት ለቀረበበት ክስ የሰጠው ማስተባበያ የለም።