(ኢሳት ዜና–መስከረም 11/2010) በሜክሲኮ በደረሰው ርዕደ መሬት ፍርስራሽ ስር የተቀበሩ ሕጻናትን ለማትረፍ የነፍስ አድን ሰራተኞች እየተሯሯጡ መሆናቸው ተነገረ።
ሕጻናትና ታዳጊ ልጆች ከርእደ መሬቱ ጋር በተያያዘ ከተደረመሰው ትምህርት ቤት ሕንጻ ስር ሆነው የአድኑን ጥሪ እያሰሙ መሆናቸው ተነግሯል።
በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 1 በተመዘገበው ርእደ መሬት እስካሁን ከ250 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የሜክሲኮው ርዕደ መሬት ያልተጠበቀና ድንገተኛ ነው።በሜክሲኮ መናገሻ ከተማ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ በርካታ ሕንጻዎች ተደርምሰዋል።
በተለይ ደግሞ የትምህርት ቤት ሕንጻዎች ተደርምሰው በርካታ ሕጻናትና ታዳጊዎች በፍርስራሹ ስር መሆናቸው ነው የተዘገበው።
ቢቢሲ እንደዘገበው በአንድ ትምህርት ቤት ብቻ 21 ልጆችና ሌሎች 5 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።
በሜክሲኮ በደረሰው ርዕደ መሬት እስካሁን ከ250 በላይ ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ ሁኔታዎች ገና እየተጣሩ መሆኑንም የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ማክሰኞ ርዕደ መሬቱ ከደረሰ በኋላ ባለፉት 2 ቀናት የነፍስ አድን ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ዘገባዎች አመልክተዋል።
በተለይ ደግሞ ኤኔሪኪው ሬብስአሜን በተባለ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በፍርስራሽ ውስጥ ያሉ ልጆችን ድምጽ እያሰሙ በመሆናቸው የነፍስ አድን ስራው ትኩረት በዚህ ስፍራ ላይ ሆኗል ተብሏል።
ወላጆች ጭንቅ ውስጥ ሆነው የጠፉ ልጆቻቸውን የአድኑልን ጥሪ እያሰሙ መሆናቸውም ነው የተነገረው።
በአንድ ሕንጻ ፍርስራሽ ስር ያለች ሕጻን ግድግዳ እየመታች በጣም ደከመኝ እያለች መሆኑም ተሰምቷል።
ልጆቹን ለማዳን ሕንጻው ሲነሳሳ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑም ታውቋል።
እስካሁን 52 ሰዎች በሀገሪቱ የባህርና የምድር ጦር አባልት እርዳታ ህይወታቸውን ለመታደግ ተችሏል።በሜክሲኮ ሲቲ 39 ሕንጻዎች መደርመሳቸው ሲነገር አጠቃላይ ስለደረሰው አጠቃላይ ጉዳት ግን የታወቀ ነገር የለም።
የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ኤኔሪኪው ፔና ኔቶ ርእደ መሬቱ ያስከተለውን ጉዳት መነሻ በማድረግ በሀገሪቱ የ3 ቀናት የሀዘን አዋጅ አውጀዋል።
በሌላ ዜና በአሜሪካ ፖርቶሪኮ ማሪያ የተባለው አውሎ ንፋስ አካባቢውን ያለ ኤሌክትሪክ ሃይል አስቀርቶታል።
ይህም ለወራት ሊዘልቅ ይችላል ተብሏል።በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ማሪያ አውሎ ንፋስ በሰአት 115 ማይል ፍጥነት እንዳለው ሲ ኤን ኤን በዘገባው አመልክቷል።