በሙስና ከተጠረጠሩ ግለሰብ 7 ሚሊዮን ጥሬ ብር ተያዘ

መስከረም ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት የአዳማ ጉምሩክ የህግ ማስከበሪያ ሀላፊ ከነበሩት ግለሰብ ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ መያዙን የፌደራል ስነ ምግባር ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጹ፡፡

ሀላፊ የነበሩት አቶ ተመስገን ስዩም 12 የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴዎችን በሌላ ሰው ስም ገዝተው ለተገዙት መኪኖች ውክልና በመውሰድ መኪኖቹን ለሌሎች ሰዎች ሸጠዋል የሚል መረጃ ቀርቦባቸዋል፡፡

ከመኪናዎቹ በተገኘ የሽያጭ ገንዘብ ደግሞ ሁለት ዶዘሮችን ለመግዛት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ለአንድ ድርጅት ክፍያ እንደፈጸሙ ተገልጿል፡፡

ግለሰቡ ክፍያ ከፈጸሙባቸው ዶዘሮች መካከል አንዱን በ7.6 ሚሊዮን ብር ለአንድ ድርጅት ያከራዩ ሲሆን ሌላውን 7.4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣውን ዶዘር ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንደነበሩ መረጃ መገኘቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡

ከግለሰቡ ወንጀል ጋር ተሳትፎ ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ነጋዴዎች ከ14 ቀን በፊት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ገንዘቡንና ንብረቱን ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው በሚል ጥርጣሬ ግለሰቡ አንድ ዶዘር የገዙበት 7.4 ሚሊዮን ብር ከተገዛበት ድርጅት እንዲመለስ ተደርጎ ኮሚሽኑ የተረከበ ሲሆን ሌላው 7.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው ዶዘር እንዲታደግ ተደርጓል፡፡

አቶ ተመስገን በፖሊስ ሲፈለጉ ከቆዩ በኋላ ከአዲስ አበባ ወደ ጋምቤላ በመሸሽ ወደ ደቡብ ሱዳን ለመግባት ሲሉ መያዛቸው ታውቋል፡፡