(ኢሳት ዜና–መስከረም 17/2010)በኦሮሚያ ክልልና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ በተፈጠረው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸውን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የማጣራት ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑንም ሃላፊው ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በጎረቤት ሶማሌ ላንድ የሚኖሩ ከሶስት ሺ የሚበልጡ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን መንግስት በይፋ አስታውቋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ለውጭ መገናኛ ብዙሃን በሰጡትና ከፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ መረዳት እንደተቻለው በግጭቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ተገድለዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች በግጭቱ ተገድለዋል በማለት በግጭቱ ከፍተኛ እልቂት መከሰቱን ያረጋገጡት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊው በሶማሌ ተወላጆች ላይም ግድያ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
የሟቾቹ ቁጥር በትክክል ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም ሲሉም ተደምጠዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ተገድለዋል የሚለው ያልተብራራ ቁጥር የሟቾቹ ቁጥር በትንሹ 100 ቢበዛ 900 ያህል መሆኑን ያመለክታል።
ከሰሜን ሶማሌ ማለትም አለም አቀፍ እውቅና ከሌላት ሶማሌ ላንድ የተፈናቀሉት ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውና በድንበር ከተማዋ ውጫሌ መስፈራቸውን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ከቶጎ ውጫሌ ተነስተው ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።
አካባቢው ከተረጋጋ ተፈናቃዮቹ ለምን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አይቆዩም ለሚለው ግን የተሰጠ ምላሽ የለም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ ኢትዮጵያውያኑ ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ ከሶማሌ ላንድ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም መንግስታዊ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
መቀመጫቸውን ሀርጌሳ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ የሕወሃቱ አባል አቶ በርሔ ተስፋዬ የኦሮሞዎቹን መፈናቀል ለመግታት ስላደረጉት ጥረት የተገለጸ ነገር የለም።