የካቲት ፳ ( ሃያ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር በመተማ ወረዳ ሻሽዬ ቀበሌ የጦር መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ ከተጠየቁት መካከል በርካቶች መሳሪያችንን አናስረክብም በማለታቸው ሲተሰሩ፣ ሌሎች ደግሞ ጫካ ገብተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በአካባቢው የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት ህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ እያስጨነቀ ይገኛል። በቀበሌው ውስጥ ታዋቂ ከሆኑት ባለሃብቶች መካከል ሼህ አዲስ፣ አቶ ደስታው፣ አንደበት ወርቃያሁና ሌሎችም የተያዙ ሲሆን፣ ባሎቻቸው ጫካ የገቡባቸው ሴቶች ደግሞ በመያዣነት መታሰራቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በአካባቢው የተሰማሩት ወታደሮች ግለሰቦች የያዙትን የጦር መሳሪያ መቀማት ብቻ ሳይሆን፣ የጦር መሳሪያውን እንዴት እንዳገኙት እንዲናገሩ ድብደባ ይፈጽሙባቸዋል። በአካባቢው “ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ በግለሰቦች እጅ ገብቷል” በሚል ሰበብ የተጀመረው ጥቃት፣ አካባቢው በውጥረት እንዲሞላ አድርጎታል።
የሽፋ ሊቀመንበር የነበረው አቶ አበረ ሙጨ ከነጻነት ሃይሎች ጋር ግንኑነት አለህ ተብሎ ተከሶ ጎንደር ከተማ ውስጥ በእስር ላይ ይገኛል።
የጦር መሳሪያ ገፈፋው የተካሄደው የክልሉ ባለስልጣናት ተጨማሪ ቀበሌዎችን ለቅማንት ብሄረሰብ አባላት ለመስጠት የአማራ ተወላጆች ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ሲያግባቡ ከሰነበቱ በሁዋላ ነው። ሰሞኑን በተለያዩ ቀበሌዎች ተደርጎ በነበረው ስብሰባ የአማራ ተወላጆች የተወሰኑ ቀበሌዎችን ለቅማንት ማህበረሰብ ለማስረከብ መስማማታቸውን በፊርማ እንዲያረጋግጡ ተጠይቀው ነበር። ይሁን እንጅ የአማራ ተወላጆች ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ ለመለያየት የሚደረገው ሙከራ ትክክል ባለመሆኑ “አንፈርምም” ያሉ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የጦር መሳሪያ የመቀማት እንቅስቀሴ እንደተጀመረ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
ህወሃት ለዘመናት አብሮ የኖረውን የክልሉን ህዝብ ለመለያየት እየሄደበት ያለው መንገድ በአካባቢው ቀደም ብሎ የተፈጠረው ግጭት ዳግም እንዳያገረሽ ስጋት እንዳላቸው ታዛቢዎች ይገልጻሉ። ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በአካባቢው ሲያስተምሩ በነበሩ አንዳንድ መምህራን ላይ የተወሰደው እርምጃ፣ መምህራን ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ አግዷቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባል የነበሩት አቶ ሙላት ፍሰሃ ባለፈው አርብ መታሰራቸው ታወቀ። የክልሉ ዘጋቢያችን እንደገለጸችው አቶ ሙላት ቀደም ብሎ የፓርቲው የሰሜን ጎንደር ወኪል ሆነው ሲታገሉ ከቆዩ በሁዋላ፣ አንድነት ፓርቲ ኢህአዴግ ወክሎ ባስቀመጣቸው በእነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ እንዲነጠቅ ከተደረገ በሁዋላ ፖለቲካዊ ተሳትፎ አልነበራቸውም።
አቶ ሙላት እስካሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ቢያመለክቱም፣ “ግለሰቡ በአደራ መልክ የመጣ እስረኛ እንጅ ማን እንዳሰረው አናውቅም” የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል።