የካቲት 22 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአማራ ፣ በድሬዳዋ፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉትን የኢሳት ምንጮች በማናገር ለማረጋገጥ እንደተቻለው የጤፍ እና የአንዳንድ የእህል ምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
በባህርዳር እና አካባቢዋ ለወትሮው 1 ሺ ብር ይሸጥ የነበረው ነጭ ጤፍ ዛሬ 1300 ብር ሲጨጥ ውሎአል። በድሬዳዋ ደግሞ 1ሺ ብር የነበረው ጤፍ እስከ 1250 ብር በመሸት ላይ ነው። በአዲስ አበባም እንዲሁ እስከ 200 ብር የሚደርስ ከፍተኛ እና ያልተጠበቀ ድንገተኛ ጭማሪ አሳይቷል። ቀደም ሲል በኩንታል 950 ብር ላይ ቆሞ የነበረው ሰርገኛ ጤፍ በድንገት 1ሸህ 50 ብር፣ እንዲሁም 1 ሺህ 50 ብር የነበረው ነጭ ጤፍ 1 ሺህ 250 ብር ገብቷል።
በተመሳሳይም አተር በኩንታል እስከ 1600 ብር፣ በርበሬ በኪሎ እስከ 70 ብር በመሸጥ ላይ ነው።
የካቲት ወር በተለምዶ የእህል ዋጋ የሚቀንስበት መሆኑን የገለጡት አንድ ነጋዴ ዘንድሮ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ በተለይ ጤፍ ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱ ግራ አንዳጋባቸው ገልጠዋል።
“መንግስት በቂ ምርት አለ ይላል፣ ገበሬው ደግሞ ምርት የለም እያለ ነው። የጭማሪው ምክንያት ሊገባን አልቻለም።” ይላሉ ነጋዴው።
በባህርዳር የእህል ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ማርቆስ ሰማኝ ገበሬው የማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የወሰደው እርምጃ ሳይሆን እንዳልቀረ ተናግረዋል። ማዳበሪያ በኩንታል 1800 ብር ገብቷል።ገበሬውም ይህንን ወጪውን ለመተካት የዋጋ ጭማሪ ያደረገ ይመስለኛል በማለት አክለዋል።
በሰሜን ጎንደር ነዋሪ የሆኑ አንድ ሸማች የችግሩ ምንጭ የመንግስት አሰራር የፈጠረው ነው ይላሉ የኑሮ ውድነቱ በደሀውና በመንግስት ሰራተኛው ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽኖ እየፈጠረ የህዝቡ ምሬትም ጎልቶ እየተሰማ ነው።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን በምግብ ምርቶች ላይ ታይቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ እንደሆነ መግለጫ ባወጣበት ማግስት እንደ ጤፍ በመሣሰሉ ምርቶች ላይ ከፍ ያለ ጭማሪ መታዬቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
በትናንት ዘገባችን በደቡብና እና በኦሮሚያ አካባቢዎች የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙን መዘገባችን ይታወሳል።የመለስ መንግስት የአገሪቱ ኢኮኖሚ 11 በመቶ እንዳደገ ቢገልጥም እስካሁን ግን በገበያው ውስጥ የሚታየውን የአቅርቦት እጥረት ሊቀርፍ አልቻለም።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide