በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን አሰሙ

(ኢሳት ዜና –ታህሳስ 3/2010)

በሊቢያ በጥቁር አፍሪካውያን በተለይም በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው የባሪያ ንግድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም አለበት ሲሉ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን አሰሙ።

በግሎባል አሊያንስና በሌሎች ሲቪክ ድርጅቶች አስተባባሪነት በተካሄደው በዚህ ሰልፍ ለኢትዮጵያውያኑ ስደትም ሆነ እንግልት ዋናው ተጠያቂ ህዝብን በመከፋፈል የሚታወቀው የህወሃት አገዛዝ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ፣በጀርመን ፍራንክፈርት፣በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያና በሌሎች ከተሞች በተካሄደው በዚህ ህዝባዊ ሰልፍ የህወሃት አገዛዝን ተባብረን ከስልጣኑ እናስወግድ የሚል መልዕክትም ተላልፏል።

በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የሊቢያ ኤምባሲ ሰልፈኞቹ የያዙትን ደብዳቤ አልቀበልም በማለቱ በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት የሰልፉ ዋና አስተባባሪና የግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን ትብብር ዳይሬክተር አቶ ታማኝ በየነና አንዲት አፍሪካዊት የሰልፉ ተሳታፊ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

በግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን ትብብርና በሌሎች ሲቪክ ድርጅቶች አስተባባሪነት በመላው አለም እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ሰልፍ በዋናነት በሊቢያ በጥቁር አፍሪካውያን በተለይም በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው የባርያ ንግድ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል የሚል መልዕክትን አንግቧል።

ሰልፉ በዋሽንግተን ዲሲ፣በጀርመን ፍራንክፈርት፣በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣በካናዳ ቶሮንቶ ፣በእንግሊዝ ለንደን፣በእስራኤል ቴላቪቭና በመላው አለም በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ሰልፈኞቹ እንደሚሉት ለዚህ ሁሉ የዜጎች እንግልትና ስቃይ ተጣያቂዎቹ የሊቢያ መንግስትና የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ናቸው።

የአፍሪካ ህብረት ዋና ስራው ምንድነው? ዜጎቹ ለባርነት ንግድ ሲቀርቡ፣በአደባባይ ሲታረዱ፣በእስር ቤት ታጉረው ሲሰቃዩ፣ሲደበደቡ ድምጹን ማሰማት ያልቻለው ለምድን ነው ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

የአፍሪካ መሪዎች እባካችሁ ዜጎቻችሁን አዳምጧቸው ጆሯችሁን ስጧቸው እናንተ የሚመች ወንበር ላይ ስለተቀመጣችሁ አትርሷቸው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

እጃቸውን በሰንሰለት አስረው የዜጎቻቸውን ስቃይ ለማሳየት የሞከሩት ሰልፈኞቹ ለኢትዮጵያውያን ስቃይና እንግልት ዋና ተጠያቂው የህወሃት አገዛዝ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ለዚህ ትውልድ ስቃይና እንግልት ብቸኛ ተጠያቂዎች እናንተ ስልጣን ላይ ያላችሁት የህወሃት አገዛዝ አባላት ናችሁ ብለዋል ሰልፈኞቹ።

በዚህ ህዝብ ደምና ገንዘብ ስልጣናችሁን ለማራዘም ብትሞክሩም ነገ ግን ዋጋ የሚያስከፍላችሁ መሆኑን እንዳትረሱ ሲሉ ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ሰልፈኞቹ በሊቢያ እየተንገላቱ ስላሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በአሁን ሰአት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይም አንስተዋል።

ወገኖቻችን አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን ሲሉም ከተማሪዎቹ ጎን መቆማቸውን አሳይተዋል።

በህዝብ ደም የስልጣን ቆይታውን እያራዘመ ያለውን የህወሃት አገዛዝን ተባብረን እናስወግደዋለን።ይሄ ደግሞ ረጅም ጊዜን የሚወስድ አይደለም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ስርአቱን ለማስወገድ በሚደረገው በማንኛውም ትግል ውስጥ ከኢትዮጵያውያኑ ጎን መቆማቸውን ሰልፈኞቹ አረጋግጠዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ሰልፈኞቹ ለሊቢያ ኤምባሲ ለማቅረብ ይዘውት የነበረውን ደብዳቤ ኤምባሲው አልቀበልም በማለት አሻፈረኝ ማለቱ ተሰምቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ የሰልፉ ዋና አስተባባሪና የግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን ትብብር ዳይሬክተር አቶ ታማኝ በየነና አንዲት አፍሪካዊት የሰልፉ ተሳታፊ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ለፖሊስ እጃቸውን ሰጥተዋል።

ተቃውሞን ማሰማት በሚፈቀድባቸው ሀገራት አንድ ሰው ተቃውሞው ተሰሚነት እንዲያገኝና ጉዳዩ ክብደት እንዲኖረው ለማድረግ በፈቃደኝነት ለፖሊስ እጅን መስጠት የተለመደ ሂደት እንደሆነ ይታወቃል።