(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2010) በሻኪሶ የለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ቦታ ስራ ማቆሙ ተገለጸ።
የአካባቢው ነዋሪ ወደ ለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ስፍራ የተዘረጉትን የውሃና የመብራት መስመሮች በመቋረጡ ስራው እንደቆመ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሜድሮክ የማዕድን ኩባንያ ኮንትራት መራዘም የተነሳ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥሎ በተለያዩ የጉጂ አካባቢዎች ሰልፎች ተካሂደዋል።
የኮማንድ ፖስት ወታደሮች ዛሬም ሁለት ሰዎች ገድለዋል።
ከነጌሌ ቦረና እስከቦሬ ያለው መስመር ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኗል። በሌላ በኩል በምዕራብ ሀረርጌ ቡርቃ ዲንቱ ሁለት ሰዎች በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በጉጂ ዞን ዛሬም ግድያ መፈጸሙን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ትላንት በአዶላ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የተቆጣው የአካባቢው ነዋሪ ዛሬ በተለያዩ የዞኑ ከተሞች ተቃውሞውን አጠናክሮ መቀጠሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የለገደንቢ የወርቅ ስራ የሚከናወንበት ቦታ ከመብራትና ውሃ አገልግሎት ውጪ መሆኑም ተገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪው ወደ ወርቅ ማምረቻው ስፍራው የተዘረጉት የውሃና የመብራት መስመሮች ላይ በፈጸመው ጥቃት አገልግሎቱ መቋረጡን ነው ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የገለጹት።
አንድ የዓይን እማኝ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ወድቆ መመልከታቸውን ገልጸው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ጥቃት ነውም ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ድርጅት ስራውን አቁሟል።
የድርጅቱ ሰራተኞች በቤታቸው የዋሉ ሲሆን መቼ ወደ ስራቸው እንደሚመለሱ እንደማያውቁ ነው የኢሳት ምንጮች ያነጋግሯቸው ሰዎች የገለጹት።
ከጥበቃ ሰራተኞች ውጪ በአሁኑ ጊዜ በለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ስፍራ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል።
ዛሬ ተቃውሞ ቀጥሎባቸው በዋሉት አካባቢዎች የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ በአስቸኳይ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቁ መልዕክቶች ሲተላልፉ እንደነበር ታውቋል።
በሻኪሶና አዶላ ክብረመንግስት መሀል ባለችው አባሎለት አካባቢ የተነሳውን ተቃውሞ በሃይል ለማስቆም የተሰማሩ የኮማንድ ፖስት ወታደሮች ሁለት ሰዎች መግደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከተገደሉት አንዱ ነጋዴ ሲሆኑ በሚያሸረክሩት መኪናቸው ላይ እንዳሉ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሌላኛው በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ርምጃ የተወሰደበት ወጣት በሞተር ሳይክል ላይ ሆኖ ሲጓዝ መገደሉን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
በሻኪሶ ዛሬ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልነበረ ታውቋል።
በ50 ኪሎ ሜትር በምትርቀው አዲዋዮ በተሰኘች አካባቢ ግን ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ የተገለጸበት ህዝባዊ ተቃውሞ መደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሁለቱም የጉጂ ዞኖች እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት አብዛኞቹ መንገዶች መዘጋታቸውም ታውቋል።
ከአዲስ አበባ ወደ ነጌሌ ቦረና በሚወስደው ዋናው መስመር ላይ ከቦሬ ጀምሮ ምንም ዓይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ የለም።
ከነጌሌ ቦረና ቦሬ ባለው 200ኪሎሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ ከተሞች የንግድም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አሁንም ውጥረቱ የበረታ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊት በብዛት መግባቱም ታውቋል።
ሻኪሶ አማኖ በተባለ አካባቢ የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት በኮማንድ ፖስቱ ዕዝ ስር ሆኖ ወደ ተለያዩ የጉጂ አካባቢዎች በመሰማራት ተቃውሞውን በሃይል ለማስቆም መዘጋጀቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በምዕራብ ሀረርጌ ቡርቃ ዲንቱ በተባለች አካባቢ በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከተገደሉት መካከል አንደኛው መምህር መሆናቸው ታውቋል።