በሶማሌ ክልል ሁለት ሱልጣኖችን ጨምሮ ከ150 በላይ ሰዎች ታሰሩ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2010) በሶማሌ ክልል ቶግዋጃሌ ሁለት ሱልጣኖችን ጨምሮ ከ150 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ተገለጸ።

ትላንት በአገዛዙ ታጣቂዎች 3 ሰዎች በተገደሉባት ቶግዋጃሌ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

በጂጂጋና በሶማሌላንድ መስመር ያለው ግንኙነት በህዝባዊው ተቃውሞ ምክንያት መቋረጡን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

100 የሚሆኑ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች አቤቱታ ለማቅረብ አዲስ አበባ መግባታቸውም ታውቋል።

ዛሬ በጂጂጋ አቅራቢያ በሚገኙት ሃሮራይና ሼድ ደር በሚባሉ መንደሮች ተቃውሞ ሲካሄድ መዋሉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በሶማሌ ባህል ሱልጣኖች የተለየ ክብር ይሰጣቸዋል።

አስታራቂ፣ ችግር ፈቺ፣ ዳኛ ተደርገው በህበረተሰቡ ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው ናቸው።

በሶማሌ ብሄረሰብ የሱልጣኖች የክብር ደረጃ ላቅ ያለ ነው። ለሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ከስልጣኑ ውጪ የሚያሳስበው ነገር የለም ይላሉ መረጃውን ያደረሱን ወገኖች።

ዛሬ ጠረፍ ላይ በምትገኘው ቶግዋጃሌ ከተማ ሁለት ሱልጣኖች በአብዲ ዒሌ ታጣቂዎች ታፍነው መታሰራቸው የሶማሌን ብሄረሰብ ባህል የመዳፈር ርምጃ በመሆኑ ብዙዎችን አስቆጥቷል።

አብዲ ዒሌ የላካቸው ታጣቂዎች ሱልጣን መሀመድ ሹግሪና ሱልጣን ዓሊ አቂል ከተባሉት ሁለቱ ሱልጣኖች በተጨማሪ ከ150 በላይ ሰዎችን ከዚያችው ቶግዋጃሌ ከተማ አፍነው ወስደዋል።

ትላንት በቶግዋጃሌ 3 ሰዎች በአብዲ ዒሌ ታጣቂዎች መገደላቸው ተቃውሞውን አባብሶታል።

ዛሬ በቶግዋጃሌ ተቃውሞ እየተደረገ ሲሆን የዓብዲ ዒሌ ታጣቂዎች በብዛት ገብተው ህዝቡን እየደበደቡት መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሽንሌ ዞንን ማዕከል አድርጎ በ11ዱም የሶማሌ ክልል ዞኖች እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ በአብዲ ዒሌ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ እየተነገረ ነው። አቶ አብዲ ተቃውሞው የሶማሌን መበልጸግ በማይፈልጉ ሃይሎች የተቀነባበረ ነው የሚል መልዕክት በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እያሰራጨ ሲሆን በውጭ ለሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችም የነዳጅ ሀብታችንን ለመዝረፍ የቋመጡ ሃይሎች ተነስተውብናል የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ለማወቅ ተችሏል።

ተቃውሞ ዛሬም ሽንሌን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ቀጥሎ ውሏል።

በተለይም በክልሉ ርዕሰ ከተማ ጂጂጋ ዙሪያ በሚገኙ ሃሮራይና ሼድ ደር በተባሉ መንደሮች ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ከስልጣን እንዲወርድ በመጠየቅ ላይ ነው።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት 100 የሚሆኑ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ለአቤቱታ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የአብዲ ዒሌ አመራር ክልሉን እየበጠበጠው በመሆኑ የፌደራል መንግስቱ መፍትሄ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ብለው ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የሀገር ሽማግሌዎችን እስካሁን ድረስ ያነጋገራቸው የመንግስት ባለስልጣን እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል።

የኢሳት ምንጮች እንደሚገልጹት የአብዲ ዒሌ ወዳጅ የሆኑት የህወሃት ጄነራሎች የሀገር ሽማግሌዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናትን እንዳይገናኙ አድርገዋል።

በሌላ በኩል ከጂጂጋ ወደ ሶማሌላንድ የተዘረጋው መስመር በህዝባዊው ተቃውሞው ምክንያት መዘጋቱ ታውቋል።

ይህ መስመር የተለያዩ የሸቀጥ ምርቶች የሚተላለፍበት መሆኑን የሚጠቅሱት ምንጮች በተቃውሞው በመዘጋቱ ከፍተኛ መስተጓጎል ተፈጥሯል።