መጋቢት ፳፫ (ሀያ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው በፍኖተሰላም እና በባህርዳር ከተማ ያለመጠለያ ተበትነው የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ፣ የክልላቸው ባለስልጣናትም ሆኑ የፌደራል መንግስቱ መፍትሄ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገለጸዋል።
በምእራብ ጎጃም ዞን በፍኖተሰላም ከተማ ሰፍረው የነበሩ ከ3 ሺ በላይ ተፈናቃዮች ከመሀል ከተማ እንዲወጡ ተደርገው፣ ባከል እየባለች በምትጠራ ገጠራማ ቀበሌ አንድ ጫካ ውስጥ እንዲሰፍሩ መገደዳቸውን በባከል ቀበሌ የሚገኙ አንድ አርሶደአደር ተናግረዋል::
ህጻናት፣ እርጉዝ ሴቶች እና በሽተኞች ሳይቀሩ ቀን በጸሀይ፣ ሌሊት በብርድ እያንዳንዷን ቀን እንዲያስልፉ መገደዳቸውን የ3 ልጆች አባት የሆኑት አባ ወራ በሀዘን ይገልጻሉ
በመጀመሪያው ዙር ተፈናቅለው በባህርዳር ከተማ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል አንድ አርሶአደር የክልሉ ባለስልጣናት ጉዳዩ የክልል ስድስት ጉዳይ በመሆኑ ክልል ሶስት አያገባውም የሚል ምላሽ እንዳገኙ ከባህርዳር ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ ከአማራ ክልል መንግስት ተስፋ አስቆራጭ መልስ ሲያገኙ ወደ ተፈናቀሉበት ክልል ተመልሰው ጥያቄ ማቅረባቸውን ይሁን እንጅ ያገኙት መልስ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ገልጸዋል
አርሶአደሩ በሌሎች ክልሎች ሄዳችሁ መስራት አትችሉም ከተባልን የክልሉ መንግስት መሬት ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጡትም ተማጽነዋል
በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን መፈናቀል የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም እያወገዙት ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በማናቸዉም የኢትዮጵያ ግዛት የመኖርና የመስራት መብት እንዳለዉና ይህም እስኪረጋገጥ ድረስ ትግሉን እንደሚቀጥል ገልጿል።
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ድርጊቱ የዐማራውን ዘር የማጥፋቱ ዘመቻ አንድ አካል ነው በማለት ኮንኗል።
በአማራ ተወላጆች ላይ የተዶለተዉ ሴራ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተዶለተ ሴራ አካል ነዉ በሚል ርእስ ድርጊቱን ያወገዘው ሌላው ድርጅት ደግሞ ግንቦት7 የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የነጻነት ንቅናቄ ነው። ንቅናቄው በአማራዉ ብሔረሰብ ላይ በማነጣጠር እየተፈጸመ ያለው የማፈናቀልና የማጥቃት እርምጃ በአገሪቱም ሆነ በአለም አቀፍ ህጎች ሁሉ በዘረኝነት ወንጀል የሚያስጠይቅ ከፍተኛ በደል ነው ብሎአል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም። ኢሳት የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ማድረግ መጀመራቸውን ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወሳል።