(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 23/2010)በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው።
ኢሳት ያነጋገራቸውና በረሃ አቋርጠው በሊቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን አደጋ ውስጥ በመሆናቸው አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ከ200 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሊቢያ የገቡት ባለፉት 10 ወራት ሲሆን በረሃ ላይ ጓደኞቻቸውን በሞት እንዳጡ በስልክ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ይድረስልንም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከጎንደር፣ ከአዲስ አበባ፣ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተሰደዱት ኢትዮጵያውያን ሊቢያ ላይ ስቃይ ላይ አረፈዋል።
ከሀገር ቤት እንዲወጡ ያደረጋቸው በእርግጥ አንድ ዓይነት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። በህወሀት መንግስት የሚደርስባቸው ጭቆና ለህይወታቸው አስጊ መሆኑን ይገልጻሉ።
በቁጥር 200 ይሁኑ እንጂ ከሀገር ሲወጡ ከዚያም በላይ ናቸው።
በረሃ ላይ በውሃ ጥምና ረሃብ የወደቁት ሊቢያም ከደረሱ በኋላም በህመምና ድብደባ ህይወታቸውን ያጡት ጓደኞቻቸው ጥቂት አይደሉም።
የበረሃውን ጉዞ አቋርጠው ሊቢያ ከደርሱት መሃል በርካታ ሴቶችም ይገኙበታል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሊቢያውን ስቃይና አሰቃቂ ግድያ እያወቁ መሄዳቸውን ይገልጻሉ።
የህወሀት መንግስት ከሚያደርስብን መጠነ ሰፊ መከራና እንግልት አይብስም ይላሉ ያነጋገርናቸው።
በተለይም በጎንደር የተነሳውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ በኮማንድ ፖስት የተዘረጋው የአፈና መዋቅር የመኖር ህልውናችንን አደጋ ውስጥ ከቶታል ያሉት የጎንደር ወጣቶች ህይወታችንን ለማትረፍ ስንል ስደትን መርጠን ሊቢያ ገብተናል ብለዋል።
አሁን የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ የተናገሩት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በመጋዘን ውስጥ ተፋፍገውና ለበሽታ ተጋልጠው እንደሚገኙና ከዚህ ጋርም ተያይዞ በተለያዩ ተላለፊ በሽታዎች ከጎናቸው ጓደኞቻቸው እያለቁ መሆኑን ተናግረዋል።
በደላሎችና በሊቢያ ታጣቂዎች የሚደርስባቸው ስቃይ ከሚችሉት በላይ እንደሆነም ገልጸዋል።
በየጊዜው እንደሚደበደቡ፣ ህክምናና ምግብ እንደማያገኙ፣ የሚገልጹት ኢትዮጵያውያን ተስፋ ቆርጠናል ህይወታችንን ታደጉን ሲሉም ጥሪ ያቀርባሉ።
በኢትዮጵያ በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአራቱም አቅጣጫ እንደሚሰደዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እስከ ደቡብ አፍሪካ በተዘረጋው የስደት ጉዞ ሀገር ጥለው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እስር ቤቶችን ያጣበቡ መሆናቸውም ይነገራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በከፍተኛ ደራጃ በማሻቀቡ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው ወጪ እያሳፈሩ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረግ መጀመራቸው ታውቋል።
አስቸጋሪውን የበረሃ ጉዞ ጨርሰው ሊቢያ የደረሱት ኢትዮጵያውያን መሄጃ የለንም፣ ወደሀገር ቤት መመለስ አንችልም። ገንዘብ የለንም። ኢትዮጵያውያን አፋጣኝ ድጋፍ ካላደረጉልን በህይወት ለመቆየት የመቻል እድላችን ጠባብ ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።