በለገጣፎ ለገዳዲ አስደንጋጭ የመሬት ዝርፊያ እየተካሄደ ነው

ጥር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው የኦሮምያ ልዩ  ዞን እየተባለ በሚጠራው  የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ የሚገኘው የአርሶአደሩ መሬት በከተማዋ ውስጥ ባልኖሩና ማንነታቸው በማይታወቅ ሰዎች ስም መያዙን ለኢሳት የደረሰው ሰነድ አመልክቷል።

ከ4 ሺ በላይ ሰዎችን ስም ዝርዝር በያዘው በዚህ ሰነድ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች የአባታቸውን ስም ብቻ በመቀያየር ከ  140 እስከ 500 ካሬ ሜትር  ቦታዎችን ይዘዋል። አለማየሁ ፣ አልማዝ፣ አለምጸሃይ፣ አሰፋ፣ አበራ  ፣ አብርሃም ፣ አበበ የሚሉ ስሞች ከ15 እስከ 30 የሚጠጉ የቦታ ካርታዎችን በስማቸው አሰርተው ይዘዋል። ግለሰቦቹ  ቦታውን ያገኙት ከ2000 እስከ 2001 ዓም ባለው የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነው።

የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በአንድ ወቅት 15 ሺ በላይ ሰዎች በህገወጥ መንገድ የቦታ ካርታዎችን መያዛቸውን የሚገልጽ መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። ለኢሳት በደረሰው ሰነድ ላይ ለማየት እንደሚቻለው አብዛኞቹ ሰዎች ቦታዎችን የሚወስዱት ጂ+2 እየተባለ የሚጠራውን ቤት ለመስራት ነው።

በከተማው የሚታየውን የቦታ ዘረፋ በተመለከተ የከተማው ነዋሪ ህዝብ በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ አድርጓል። የኦሮሚያ ክልል ችግሩን ለመፍታት ቃል ቢገባም የከተማዋ አመራሮች ወርደው በሌሎች እንዲተኩ ከማድረግና የተተኩትም ሰዎች ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈጸም ው   የተለወጠ ነገር አለመኖሩን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በለገጣፎ ለገዳዲ በኮምኒኬሽን ሰራተኛነት ሲያገለግል የነበረው የገዢው ፓርቲ አባል  ወጣት መኮንን ተስፋየ በከተማዋ ውስጥ የሚፈጸመውን ዝርፊያ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን በማጋለጥ በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ከቆየ በሁዋላ፣ በመጨረሻም ህይወቱን ለማትረፍ ሲል በቅርቡ ከአገር ተሰዷል። ወጣት መኮንን እንደሚለው እብዛኞቹ የከተማዋ ቦታዎች በባለስልጣናት የተቸበቸቡ ናቸው።

በሙስና የተከሰሱት የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ምክትል ሃላፊ አቶ ገብረውሃድ ወልደ ጊዮርጊስ በዚሁ በለገጣፎ ለገዳዲ የቦታ ካርታ በብዛት ይዘው ከተገኙት መካከል ናቸው።

የአዲስ አበባ መስተዳድር እነዚህን ከተሞች ከአዲስ አበባ ጋር ለመቀላቀል ቢያቅድም፣ የኦሮምያ ክልል ፈቃደኛ ባለመሆኑ እስካሁን አልተሰካም። የኦሮምያ ክልል ከእንግዲህ ለአዲስ አበባ የምንሰጠው መሬት የለም በሚል አቋሙ በመጽናቱ የፌደራሉ መንግስት የቤቶች ልማት እቅድን ለመተግበር እየተሳነው መጥቷል። ከወጣት መኮንን ተስፋየ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ በቅርቡ ይቀርባል።