በሃረር ታስረው ክሚገኙት  ነጋዴዎች መካከል የተወሰኑት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ግንቦት ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በሃረር የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ንብረታቸው የወደመባቸው  ነጋዴዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸው ከሽብረተኝነት ወደ ባንዲራ ማቃጠል፣ ንብረት ማውደም እና አመጽ ማስነሳት መለወጡ ተነግሯቸዋል።

ከእሰረኞቹ መካከል 2ቱ በመታወቂያ ዋስ እንዲፈቱ ሲደረጉ፣ 20 ዎቹ እስረኞች ደግሞ ባንዲራ አውርዶ በማቃጠል፣ 500 ሰዎችን አስተባብረው አመጽ በማስነሳት፣ የመንግስትን ስራ በማስተጓጎልና የግለሰብና የመንግስት ንብረት በማውደም ክስ ቀርቦባቸዋል። የእያንዳንዱ ክስ የቅጣት ጣራ ከ15 አመታት በላይ የሚያሳስር በመሆኑ እስረኞቹ የዋስ መብት እንደሌላቸውና ጉዳያቸውን በእስር ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ውስኗል።

በዛሬው ፍርድ ቢኒያም ጌታቸው፣ ለይላ አሊ አህመድና ዙቤር አህመድ የተባሉት የክስ ቻርጅ የደረሰቻው ሲሆን ሌሎች 17ቱ ግን የክሱ ዝርዝር አልደረሳቸውም። ለይላ አህመድ የተባለችው ነጋዴ በእስር ቤት ማህጸኗ ላይ ባደረሱባት ድብደባ በህመም እየተሰቃየች እንደምትገኝ መዘገባችን ይታወሳል።

ቢኒያም ጌታቸው የተባለው ወጣት ደግሞ የኮምፒዩተር ጥገና ባለሙያ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የሃረር ፖሊስ ጽህፈት ቤትን ኮምፒይተሮች በመጠገን፣ ያልተከፈለው 12 ሺ ብር እንዳለና ምናልባትም የእስሩ ምክንያት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል። ቢኒያምን በምንም አይነት ወንጀል መጠርጠር እንደማይችል የሚናገሩት ጉዳዩን የሚከታተሉ ምንጮች፣ ፖሊስ ኮሚሽን የራሱን ችግር ለመሸፋፈን ሲል እንዳሰረው አስተያየት ይሰጣሉ።

ድብደባ የተፈጸመባትና ዋስትና የተከለከለችው ለይላ ደግሞ  የመንግስትን ባለስልጣናት “እናንተ ናችሁ ቃጠሎውን ያስነሳችሁት ፣ ሌቦች” ብላ በመሳደቡዋ መታሰሩዋን ምንጮች ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን አቃቢ ህግ ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።