በሃረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ግምጃ ቤት በተገኘው አጽም የተጠረጠሩ የፖሊስ አዛዦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ውሳኔ ተላለፈ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 13 ቀን 2010 ዓ/ም ) በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ግምጃ ቤት የተገኙትን አጽሞች ተከትሎ ዛሬ አርብ ሃምሌ 13 ቀን 2010 ዓም የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አበበ መብራቱ ፣ ም/ል ፕሬዚዳንት ጋቢሳ ተስፋዬ፣ ሃብሊ ሊቀመንበር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ በኦህዴድ የሃረሪ ክልል ሊ/መንበር በአቶ ጀግናውና በሌሎችም ባለስልጣኖች በተመራው መድረክ ላይ፣ የቄሮ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ አባ ገዳዎችና የመንግስት ተወካዮች በተገኙበት ከፍተኛ ክርክር የተደረገ ሲሆን፣ በመጨረሻም ከአመጹ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩት የህብሊ ምክትል ሊ/መንበር አቶ ነብል መሃዲ ፣ የቀድሞው የሃረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣አቶ አብዱልፈታህ አብዱልቃድር፣ የሃረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ነስሩ አሊ፣ የክልሉ ልዩ ሃይል ዋና አዛዥ ኮማንደር አሊ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንዲጣራባቸው በሙሉ ድምጽ ተወስኗል።
በአስከሬኑ ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ለመከታተል 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል። ለሰዎቹ ሃውልት የሚሰራበት ሁኔታም እንዲመቻች በፕሬዚዳንት ጽ/ቤት በነበረው ስብሰባ ላይ ወስነዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሃረሪ ክልል ህገመንግስት እንዲሻሻል መወሰኑ ታውቛል።