መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሃረር በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የንግድ ቤቶች መቃጠላቸውን ተከትሎ፣ በህዝቡና ክልሉን በሚመራው የሃረሪ ሊግ መካከል የተፈጠረው ከፍተት እየሰፋ መሄድ የብሄር ግጭት ሊያስነሳ ይችላል በማለት ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ክልሉን የሚያስተዳድረው የሃረሪ ሊግ ” መጤዎች ከከተማችን ውጡ” የሚሉ ቅስቀሳዎችን ከጀርባ ሆኖ በማሰራጨትና የንግድ ቤቶችን በማቃጠል ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ የኖረውን የሃረርን ህዝብ በመከፋፈል የብሄር ግጭት ለማስነሳት እየጣረ ነው። እነዚሁ ባለስልጣናት ለህዝቡ ያሰቡ በማስመሰል የሚያሰራጩት ቅስቀሳ፣ በተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ፍርሃትና አለመረጋጋት እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
የካቲት 30 ቀን፣ 2006 ዓም በሸዋ በር የንግድ ማዕከል የተነሳውን እሳት ተከትሎ ህዝቡ ሲያሰማው የነበረው መፈክር ፣ በክልሉ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በህዝቡ ቁጣ የተደናገጠው አስተዳደሩ በተለያዩ የወረዳ እስር ቤቶች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን አስሮ እያሰቃየ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
አስተዳደሩ መጀመሪያው ቃጠሎ የተነሳው ሳባ በምትባል ሰው ምግብ ቤት ውስጥ ነው በሚል ሳባ የተባለችውን ሰው አስሮ መግለጫ በሰጠ በሳምንቱ በመብራት ሃይል የንግድ ማእከል በድጋሜ ቃጠሎ የተነሳ ሲሆን፣ ሁለተኛው ቃጠሎ የተነሳው በኤሌክትሪክ ችግር ነው በሚል የ ሀረሪ መብራት ሃይል የቴክኒክና ስልጠና ሃላፊ የሆኑትን አቶ ገብሬ ቶላን ጨምሮ ሙላቱ ብዙ፣ ሀይሉ ክንፈና አቡሽ የተባሉ የድርጅቱ ሰራተኞች እንዲታሰሩ ተደርጓል።
መስተዳድሩ ሳይውል ሳያድር ድርጊቱ የሽብርተኞችና በከተማዋ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚሰሩ ሃይሎች ያስነሱት ነው በሚል በመስተዳድሩ ምክትል ፕሬዚዳንት በኩል መግለጫ መስጠቱ ህዝቡን ይበልጥ ግራ ማጋባቱንና ከቃጠሎው ጀርባ መስተዳድሩ አለበት የሚለውን ጥርጣሬ ከፍ አድርጎታል።
መስተዳድሩ በስም ያልጠቀሳቸውን አሸባሪዎች ለማውገዝ ዛሬ በጠራው ሰልፍ በግዳጅ ከወጡት የመንግስት ሰራተኞችና ከገጠር በአይሱዙ መኪኖች ተጭነው ከመጡት ሰዎች በስተቀር አብዛኛው የከተማው ነዋሪ በሰልፉ ላይ ሳይገኝ ቀርቷል። ትናንት ምሽት ጀጎል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ህዝቡ በሰልፉ ላይ እንዳይገኝና በመንግስት ማደናገሪያ እንዳይታለል የሚቀሰቅስ በራሪ ወረቀት ሲበተን አምሽቷል። እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች በግዳጅ እንዲሰበሰቡ ተደርጎ በቃጠለው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ እንዲሁም መንግስት እሳቱን ሆን ብሎ አላስነሳውም ብለው እንዲመሰክሩ እንዲሁም ክልሉ የሚሰራው ለአንድ ብሄር ሰዎች ነው እየተባለ የሚባለው ትክክል አለመሆኑን መስክሩ ተብሎ እንደተነገራቸው ለማወቅ ተችሎአል።
ዛሬ ሰልፍ እንዲወጣ የታዘዘው ነዋሪ ” ሀረር የሽብርተኞች መናኸሪያ አትሆንም፣ የብሄር ብሄረሰቦች ግጭት የሚፈልጉትን እንቃወማለን” የሚሉ መፈክሮችን አሰምቷል። የመስተዳድሩ ባለስልጣናት “በሃረር አልሸባብ፣ አሊተሃድ፣ አልቃይዳ እንዲሁም ጸረ-ሰላም ሃይሎች በመግባታቸው ህዝቡ ከጎናችን ሆኖ ይተባበረን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ከመንገድ ላይ እያፈሰ ያሰራቸውን በርካታ ሰዎች በድብደባ ማሰቃየቱና በጊዜ ቀጠሮ እያሳበበ ሊለቃቸው አለመፈለጉ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል።
በሀረር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በተነሳው ቃጠሎ ከ 20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ከ800 ያላነሱ ነጋዴዎች ንብረት መውደሙን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የክልሉን ባለስልጣናት ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።