ጥቅምት ፳፯(ሃያ ሰባት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከማንነት ጋር በተያያዘ አንዴ ሲሞቅ ሌላ ጊዜ ሲቀዘቅዝ የነበረው የቁጫ ተቃውሞ በዛሬው እለት በሰላም በር ከተማ ተጠናክሮ መካሄዱን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
ዛሬ ተቃውሞውን ያካሄዱት ተማሪዎች ሲሆኑ ፣ ተማሪዎችም ላቀረብነው ጥያቄ መልስ የማይሰጠን ከሆነ ትምህርት አንማርም ብለዋል።
ተቃውሞውን አስተባብረዋል የተባሉ መምህራንም በአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተው ተቃውሞን የመሩትን እንዲያጋልጡ ተጠይቀዋል። ልዩ ሀይል ከተማዋን ተቆጣጥሮ በተማሪዎች ላይ ድብደባ የፈጸመ ሲሆን 15 የሚሆኑ ወጣቶችም ተይዘው ታስረዋል። ተማሪዎቹ በቋንቋችን እንማር የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያሰሙ ውለዋል።
ከዚህ ቀደም ከ60 ያላነሱ ሰዎች ታስረው መፈታታቸው ይታወቃል። 40 የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ደግሞ ከስራ እንዲባረሩ ተደርጓል። እንዲሁም የወረዳው ነዋሪዎች መረጃዎችን ለመለዋወጥ ይጠቀሙባቸዋል ያላቸውን 160 ባጃጅ እየተባሉ የሚጠሩ ተሽከርካሪዎችን አስሯል።
በወረዳው ውስጥ ባሉ 26 ቀበሌዎች ያለው ውጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩም ታውቋል።