ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የ2005 ዓ.ም አገራዊ ረቂቅ በጀት በዛሬው ዕለት ለፓርላማ አቀረበ፡፡
የቀረበው አጠቃላይ በጀት 137 ቢሊየን 836 ሚሊየን 47 ሺህ 105 ብር ሲሆን ይህ ረቂቅ በጀት በገቢና ወጪው መካከል የ26 ቢሊየን 634 ሚሊየን 956 ሺህ 84 ብር ጉድለት ያሳያል፡፡ይህ ጉድለት በ2005 ዓ.ም ከተመደበው ጠቅላላ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች ማለትም ለደመወዝና ሥራማስኬጃ ከተያዘው 26ቢሊየን 811ሚሊየን 47 ሺህ 670 ብር ጋር ተቀራራቢ ሆኗል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ ዛሬ ረቂቅ በጀቱን ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት ያጋጥማል የተባለውን የበጀት ጉድለት ለማካካስ 13 ቢሊየን 10ሚሊየን 893 ሺህ 278 ብር ከውጪ በሚገኝ ብድር፣13 ቢሊየን 624 ሚሊየን 62 ሺህ 807 ብር ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
በያዝነው 2004 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ የተሰበሰበው ጠቅላላ ገቢ ፣ ዕዳ ቅነሳን ጨምሮ ፣ 66 ቢሊየን 754 ሚሊየን ሲሆን ጠቅላላ ወጪው ደግሞ 72 ቢሊየን 476 ሚሊየን በመሆኑ የ5 ቢሊየን 722 ሚሊየን ብር የበጀት ጉድለት መታየቱን ለፓርላማው የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡
ለቀጣይ ዓመት ከተያዘው በጀት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ከተባሉት ተቋማት መካከል መከላከያ 6.5 ቢሊየን ብር ሲበጀትለት ፍትህና ደህንነት 2 ቢሊየን 318 ሚሊየን ብር ተይዞለታል፡፡
በተጨማሪም ለመደበኛ ወጪ ብቻ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት 289 ሚሊየን ብር፣ፌዴራል ፖሊስ 877 ሚሊየን፣የኢንፎርሚሸን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ 128 ሚሊየን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡
ከፍተኛ ተጨማሪ በጀት ጠይቀው ከተፈቀደላቸው መካከል የመንግስት መገኛኛ ብዙሃን ማለትም የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ይገኙበታል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራ ሲሆን ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ፓርላማው ለክረምት ዕረፍት ከመበተኑ በፊት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መንግስት በዚህ አመት ለደህንነት ተቋማቱ ከፍተኛ በጀት መመደቡ በየጊዜው የሚታዩትን ግጭቶችና ተቃውሞዎች ለመቆጣጠር ያመቸው ዘንድ ሊሆን ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide