በማላዊ ሊካሄድ የነበረው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር ተወሰነ

ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ስብሰባው ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር የተደረገው፤ ማላዊ  በ ዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የ እስር ማዘዣ የወጣባቸውን የሱዳኑን ፕሬዚዳንት ለመቀበል ፈቃደኛ  ባለመሆኗ ነው።

“አገራችን ስብሰባውን የምታዘጋጅ ከሆነ  ኦማር ሀሰን አልበሽር እንዲሳተፉ አንፈቅድም፤ምክንያቱም በዓለማቀፉ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት እና በጦር ወንጀለኝነት የሚፈለጉ ሰው ናቸው” ብለዋል- የማላዊ ፕሬዚዳንት።

በ አዲስ አበባ የ አፍሪካ ህብረት አምባሳደር ፈርዲናንድ ሞንታቾ  ዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን  በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ይገባል በማለት ይከሳሉ።

በአልበሽር ላይ የተመሰረተውንም ክስ ፖለቲካዊ  መነሾ ያለው ነው በማለት ያስተባብላሉ- አምባሳደር ፈርዲናንድ።

በዓለማቀፉ የጦር ወንለኞች ፍርድ ቤት ህግ መሰረት፤  ማላዊን ጨምሮ  የ ፍርድ ቤቱ አባል አገራት  የ እስር  ማዘዣ የወጣባቸውን ተፈላጊዎች የማሰር ሀላፊነት አለባቸው።

ማላዊ  በዚህ  ምክንያት  ስብሰባውን ለማዘጋጀት ፈቃደኛ እንዳልሆነች ማሳወቋን ተከትሎ  የ አፍሪካ ህብረት አባል አገራት ባደረጉት ውይይት፤ 19 ኛው የህብረቱ መደበኛ ስብሰባ  ቀደም ሲል  በተያዘለት  ቀን  በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ወስነዋል።

ማላዊ  የ አይ.  ሲ. ሲን  የ እስር ማዘዣ ወደ ጎን በማለት   በምታዘጋጀው ስብሰባ ላይ   አልበሽር ይሳተፉ ዘንድ  እንድትፈቅድ  ህብረቱ ከፍ ያለ ግፊት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል።

ሆኖም ማላዊ ከአቋሟ ባለመነቃነቋ ስብሰባው ከሊሉዌንጎ ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር ተወስኗል።

በሁኔታው የተበሳጩት  የህብረቱ አምባሳደር፦”አይ. ሲ. ሲ እየሠራ ያለው ነገር ሊገባኝ አልቻለም፤ ሁሉጊዜ ስብሰባችን በደረሰ ቁጥር  ይረብሸናል”በማለት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

“ለምን ይህን ሲኒማቸውን፣ይህን ቴ አትራቸውን እና ይህን ጭውውታቸውን አቁመው ስብሰባችንን በሰላም እንድናካሄድ  አይተውንም?” ሲሉም አክለዋል-አምባሳደር ሞንትቾ።

የ ዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ጠበቃ  ግን  የሱዳኑን ፕሬዚዳንት ለማሰር ፈቃደኛ ላልሆኑት አገሮች   ለጋሾች  እርዳታቸውን እንዲያቆሙ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የማላዊ ፕሬዚዳንት ጆይሴ ባንዳ ፤ አገራቸው አልበሽርን ብታስተናግድ ከለጋሽ አገሮች ጋር ልትቀጠያየም  ትችላለች  የሚል ከፍ ያለ ስጋት እንዳላቸው መግለፃቸውን ቢቢሲ አስታውሷል።

“ማላዊ  ዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤትን  ትቀበላለች፤ የውጪ እርዳታ ፍሰትም እንዲቋረጥና እንዲስተጓጎል አትፈልግም” ነበር ያሉት ጆይሴ ባንዳ።

ማላዊ ፤አልበሽርን  ለመቀበል አለመፍዷን ተከትሎ  ካርቱም  መጪው የ አፍሪካ ህብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መጠየቋ ይታወሳል። አይ.ሲ.  ሲ   በአልበሽር ላይ  ያወጣውን የ እስር ማዘዣ  ከሚቃወሙት አገሮች መካከል፤ ቻድ፣ኬንያ፣ጁቡቲ ፣ ኬንያ  እና ኢት ዮጵያ ይጠቀሳሉ።

ይሁንና አልበ ሽር ከመከሰሳቸው ከወራት በፊት በመንታ መስፈርት ወይም በደብል ስታንዳርድ አቋማቸው የሚታወቁት  የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር  መለስ  ዜናዊ – ከአሜሪካ  ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት የምሥጢር ስብሰባ ፤ አሜሪካ በሱዳን ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ እና  የ አካባቢውን ሰላም ማረጋጋት የምትችለው፤  አልበሽር በ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት እንዲከሰሱ ስታደርግ ነው  የሚል አስተያዬት መሰንዘራቸውን ዊክሊክስ ማጋለጡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide