ቀነኒሳ በቀለንና ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ ታዋቂ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከውድድር ታገዱ
ጥር 11 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰለች መልካሙ ፣ ስለሺ ስህንና ሌሎች በአለማቀፍ ውድድሮች ከወርቅ እስከ ነሀስ ያገኙ አትሌቶች ከውድድር እንዲታገዱ የተደረገው በመጪው መጋቢት ወር በሚካሄደው አለማቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር እና ለለንደን ማራቶን ልምምድ እንዲያደርጉ ተጠይቀው በጊዜው ሪፖርት ለማድረግ ባለመቻላቸው ነው ተብሎአል።
35 አትሌቶችን በአንድ ጊዜ ሪፖርት አላደረጉም በሚል ማገድ አሳማኝ ሆኖ አልተገኘም።
አትሌቶቹ ፕሮፌሽናል እንደመሆናቸው የወድድርና የስልጣና ጊዜያቸውን ጠንቅቀው የሚያዉቁ ሆነው እያለ፣ ሪፖርት ባለማድረግ ታገዱ ማለት ሌሎችን የውስጥ ችግሮች ለመሸፋፋን ተብሎ የተሰጠ ምክንያት እንዳይሆን ያሰጋል ሲል አንድ ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገ የሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኛ ተንታኝ ለኢሳት ተናግሯል።
ፌዴሬሽኑ ውስጥ ይህ ነው የማይባል ችግር አለ፣ ከሁሉም በላይ በፖለቲካው ውስጥ የሚታየው ዘረኝነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር በፌደሬሽኑ ውስጥ በትክክል ይንጸባረቃል፤ አትሌቶችም እንዲህ አይነቱን አሰራር ሲቃወሙ ቆይተዋል ብለዋል።
አትሌቶቹ ምክንያታቸውን ለማቅረብ ባለመቻላቸው በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛውን ምክንያት ለማወቅ የእነሱን መልስ መጠበቅ ግድ ይላል ብሎአል።
2012-01-20