(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2010) በሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን የተጀመረው ተቃውሞ ወደ ቀብሪ በያህ፣ ደገሀቡር፣ቀብሪዳሃርና ወደሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ በመካሄድ ላይ መሆኑ ታወቀ።
በጅጅጋ ዙሪያ ባሉ መንደሮችም ተቃውሞው ቀጥሏል።
በአብዲ ዒሌ የሚታዘዘው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶችን እያፈነ በመውሰድ ላይ መሆኑንም የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
የሽንሌ ዞን አስተዳደር የተዘጋ ሲሆን በዞኑ የሚገኙ የአራት ወረዳ መንግስታዊ መዋቅሮችም መወገዳቸው ታውቋል።
በአንድ ዞን የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደሌሎቹ መዛመቱን የሚያሳዩ መረጃዎች ለኢሳት ደርሰውታል።
በተለይም በደገሃቡር፣ ቀብሪበያህና ቀብሪደሃር አካባቢዎች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ ሲሆን ዛሬ በእነዚህ አካባቢዎች ወጣቶች መፈክር በማሰማት የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ከስልጣን እንዲወርድ ጠይቀዋል።
ተቃውሞ በጀመረባት የሽንሌ ዞን መንግስታዊ መዋቅሮች ከእንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
በተለይም አረር፡ ኤረርባና ሃደጋሎ የተባሉ ወረዳዎች የመንግስት አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መፍረሳቸውን የደረሰን ዜና አመልክቷል።
የህዝቡ ርምጃ ለማስቆም ተጨማሪ የክልሉ ልዩ ሃይል ሰራዊት ወደ ሽንሌ ከተማ የገባ መሆኑም ታውቋል።
በሽንሌ ዞን የተጠናከረው ህዝባዊ ንቅናቄ ትላንት በድሬዳዋ የተደረገው ድርድር መክሸፉን ተከትሎ ሌሎች አካባቢዎችንም በመጨመር ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ትችሏል።
በትላንቱ ድርድር የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲቆም እንዲያደርጉ ለሀገር ሽማግሌዎቹ በማስፈራራት ጭምር ጫና የፈጠረ ቢሆንም የሀገር ሽማግሌዎቹ ባለመስማማታቸው ድርድሩ መፍረሱን መዘጋባችን የሚታወስ ነው።
የድርድሩ መፍረስም በክልሉ የሚካሄደውን ተቃውሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጉን ነው ዛሬ ከተለያዩ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች የሚያመለክቱት።
በሽንሌ አስቡሊ በተባለች ከተማ ዛሬ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ መሆኑም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከሽንሌ በተጨማሪ በአራት ሌሎች ዞኖች ህዝባዊ ተቃውሞው መስፋፋቱ ታውቋል።
በዋነኝነት ለስቃይና መከራ የዳረጋቸውን የአብዲ ዒሌን አስተዳደር ለማውገዝ ሲሆን ተቃውሞውን የሚያስተባብሩት ባርባራት በሚል የሚታወቁት የሶማሌ ክልል ወጣቶች መሰረታዊ የሆነ ለውጥ እስከሚመጣ ተቃውሞ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ።
ባለፉት 10 ዓመታት የሶማሌ ክልልን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩትና ከህወሀት ጄነራሎች ጋር ባላቸው የቀረበ ወዳጅነት ተቀናቃኞቻቸውን በመግደል፣ በማሰርና ከሀገር እንዲሰደዱ በማድረግ በፈላጭ ቆራጭነት የዘለቁት አቶ አብዲ ዒሌ ከሽንሌ ዞን የተነሳውን ተቃውሞ የስልጣን ጥማት ያሰከራቸው የሽንሌ ዞን አንዳንድ ሰዎች ያቀናበሩት ተቃውሞ ነው በማለት ያጣጥሉታል።
የቤተዘመድ ጉባዔ በሚል የሚጠራው የአብዲ ዒሌ ካቢኔ ሌላውን የሶማሌ ጎሳ በማግለል የእሳቸውን ቤተሰብና በጋብቻ የሚዛመዳቸውን ሰብስበው ስልጣን መስጠታቸው ለተቃውሞ አንዱ ምክንያት ነው።
ዋናው ግን በክልሉ የተንሰራፋው ድህነት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት መሆኑን ተቃውሞን የሚያስተባብሩ ወገኖች ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ውጭ ሀገር በሚገኝ ዘመዳቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምክንያት ታስረው የሚገኙት ዶክተር ሀሰን አብዱላሂ ባዴ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑ ታወቋል።
እኚህ የሶማሌ ክልል ተወላጅ አንድ ዘመዳቸው በውጭ ሀገር በሚያደርገው የፖለቲካ ተሳትፎ የተነሳ ጄል ኦጋዴን በተሰኘ የማሰቃያ እስር ቤት ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ነው ሲል የሶማሌ ክልል ተወላጆች የአክቲቪስቶች መረብ ለኢሳት ገልጿል።