(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 2/2011)በደቡብ አፍሪካ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ፍትህ ድምጻቸውን በማሰማት የሚታወቁት ሼህ ወርቁ ኑሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ሼህ ኑሩ ላለፉት 20 ዓመታት በደቡብ አፍሪካ በሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል አንስቶ በዋና ዋና የፖለቲካ ንቅናቄዎች ውስጥ ሚናቸው በጉልህ የሚጠቀሰው ሼህ ኑሩ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የነጻነት አርማ ተደርገው እንደሚታዩም ለማወቅ ተችሏል።
ሼህ ኑሩ የቀብር ስነስርዓታቸው በደቡብ አፍሪካ በዛሬው ዕለት መፈጸሙን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል የአንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም አባተ የቀብር ስነስርዓትም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መፈጸሙ ታውቋል።
ከሃገር የወጡት ህወሀት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር።
ኢሳው ለተሰኘ አንድ መጽሄት በሰጡት ቃለመጠይቅ ከሀገር የወጡትበትን ምክንያት ሲያብራሩ ጫካ የነበሩት የሀገር አጥፊዎች መንግስት ሆነው ኢትዮጵያን ሲያጠፏት ማየት አልፈልግም በማለት ነበር።
በኬንያ አድርገው ስደት የወጡት አዛውንቱ ሼህ ኑሩ ወርቁ እስከደቡብ አፍሪካ የተዘረጋውን አስቸጋሪና አደገኛ የስደት ጉዞ አልፈው ደቡብ አፍሪካ መኖር ከጀምሩ 20 ዓመታትን አስቆጥረዋል።
ስደት ሲወጡ እድሜአቸው 60ዓመት ነበር። የአዛውንት ጉልበታቸው ቢደክምም የኢትዮጵያን ህመም ከማይ ብለው በእድሜአቸው የማይሞከረውን ሞክረው ደቡብ አፍሪካ ደረሱ።
ሼህ ኑሩ ወርቁ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ አባት ብቻ አልበሩም። የነጻነት አርበኛ፣ የትግል አጋር፣ የጽናት ተምሳሌት ሆነውም ቆየተዋል።
ስለኢትዮጵያ የነጻነት ጥያቄ በተጠራ ሰልፍ ላይ ሼህ ኑሩን ማጣት የማይታሰብ ነው ይላሉ እሳቸውን የሚያውቁ ሁሉ።
ስለኢትዮጵያ በሚጮህ መድረክ ላይ ሼህ ኑር አንድም ቀን ሳያጓድሉ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው፣ የሀገር ቤቱን ስቃይና መከራ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
ስለኢትዮጵያ በተጠሩ ሰልፎች ዘር ቀለም ሃይማኖት ሳይለዩ መለያቸውን ሰንደቅዓላማ ይዘው መገኘት ሀገራዊ ግዴታቸው አድርገው በመውሰድ ሲሳተፉ ቆይተዋል።
ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል፣ ከጋምቤላ አኝዋኮች ጭፍጨፋ፣ ከኦሮሚያ ህዝባዊ ንቅናቄ፣ ከአማራው የተጋድሎ ታሪክ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በሚደርስ በደል ለሚደረግ የአጋርነትና የድጋፍ ሰልፍ ሼህ ኑሩን ቀድሞ የሚገኝ አይኖርም።
ስለኢትዮጵያ በተባለበት፣ በተነገረበት፣ ቦታ ሁሉ ፈጥነው የሚገኙ ሀገር ወዳድ ነበሩ።
ሼህ ኑሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ በስደትም ይሁን በሌላ መንገድ ሲገቡ በመርዳት በማቋቋም ወገናዊ ፍቅራቸውን የማይነፍጉ እንደሆኑም በቅርበት የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
ለታመሙ የሚረዱ፣ የታሰሩትን ገንዘብ ከፍለው የሚያስፈቱ በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ማህበር ውስጥ ተሳትፈው ገንዘብና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ የሚያበረክቱ ናቸው ይሏቸዋል።
እርጅና ሳያሸንፋቸው፣ ለአቅም መድከም እጅ ሳይሰጡ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ስለኢትዮጵያ ነጻነት ሲጮሁ የኖሩ አርበኛ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ትላንት በ86 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በዛሬው ዕለትም እዚያው በደቡብ አፍሪካ የቀብር ስነስርዓታቸው መፈጸሙን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተያያዘ ዜና አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስዩም አባተ የቀብር ስነስርዓት በዛሬው ዕለት መፈጸሙ ተገልጸ።
ለግማሽ ክፍለዘመን በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ስማቸው በጉልህ የሚጠቀሰው አሰልጣኝ ስዩም አባተ ቅዱስ ጊዮርጊስን በተጫዋችነት፣ የኢትዮጵያ ቡናን በአሰልጣኝነት ያገለገሉበት ዘመን ውጤታማ ተደርጎ በታሪክ ይጠቀስላቸዋል።
አሰልጣኝ ስዩም ባደረባቸው ህመም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ህክምናቸውን የተከታተሉ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ ሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን የቀብር ስነስርዓታቸው መፈጸሙ ታውቋል።