የቤንሻንጉል ተፈናቃይ እናቶች በመጠለያ ውስጥ ልጆቻቸውን ተገላገሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 2/2011) ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቅለው በኦሮሚያ ክልል ከተጠለሉ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ20 በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች በመጠለያ ውስጥ መገላገላቸው ታወቀ።

ሌሎች 53 ወራቸው የገባ ነፍሰ ጡሮች የመውለጃ ጊዜያቸውን እየጠበቁ መሆናቸው ተመልክቷል።

የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ነፍሰ ጡሮችንና እመጫቶቹን በመንከባከብ ላይ መሆኑን መረጃው አመልክቷል።

የቤንሻንጉል ክልል ካማሼ ዞን ባለስልጣናት ከስብሰባ ሲመለሱ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ በካማሼ ዞን ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በተወሰደ የአጸፋ ጥቃት ወደ መቶ ሺ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

አንዳንድ ሪፖርቶች እንዳመለከቱትም ወደ መቶ የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

በዚህ መልክ የተፈናቀሉት ሰላማዊ ሰዎች ውስጥ 80ሺ ያህሉ ምስራቅ ወለጋ ነቀምት ከተማ በ9 መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙም ተመልክቷል።

ከመስከረም 10/2011 ጀምሮ በነቀምት መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙት ተፈናቃዮች 20 ነፍሰጡር እናቶች ልጆቻቸውን በመጠለያው ውስጥ መገላገላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

ሌሎች 53 ነፍሰ ጡር እናቶችም ወራቸው ገብቶ የመውለጃ ቀናቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

የነቀምት ሆስፒታል እመጫቶቹንና ነፍሰጡር እናቶቹን ለመንከባከብ ልዩ ማቆያ ማዘጋጀቱም ተመልክቷል።

ከተፈናቃዮቹ ውስጥ በተፈናቀሉበት ወቅት መንገድ ላይ የወለዱ እናቶች መኖራቸውም ይታወሳል።

የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ያነጋገራት ታንጉት ይመር የተባለች ተፈናቃይ ሰለሞን ብላ የጠራችውን ልጇን መንገድ ላይ መገላገሏን ገልጻለች።

ሌሎች ደግሞ በወለዱ ማግስት አዲስ ልጅ ይዘው በመከራ ውስጥ እያሳለፉ መሆናቸውም ታውቋል።

በካማሼ ዞን ያለውን ጸጥታ ለማረጋጋት የመከላከያ ሰራዊቱን የጨመረ ሰላም የማስጠበቅ ስራ በመሰራት ላይ ቢሆንም ሰብሎችንና ቤቶችን የማቃጠል ተግባር መቀጠሉን ተፈናቃዮቹ ገልጸዋል።