(Aug. 15) የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሰወር የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል። ሲ ኤን ኤን ዘወትር ከመድረክ የማይጠፉት አቶ መለስ ዜናዊ፤ ከሁለት ወራት በላይ የት እንዳሉ አይታወቅም ሲል ዘግቧል።
መንግስት በሚያሰራጨው የተቆጠበ መረጃ መላምቶች እየሰፉ መቀጠላቸውን፤ በሀገሪቱ ፍርሀት መንገሱንም ሲ ኤን ኤን ዘርዝሯል።
“ስለ ጠ/ሚ/ሩ ሁኔታ ለማውራት ፍርሀት አለ። ይህ በሕግ ሳይሆን በሀይል የሚመራ ሀገር ነው።” በማለት ለሲ ኤን ኤን ዘጋቢ ፌይት ካርሚ አስተያየቱን የሰጠው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነ ሚካኤል የተባለ የ30 ዓመት ወጣት ነው።
በመሸታ ቤት በታክሲ እና በካፌዎች ሁሉም ስለጉዳዩ እንደሚያወራ፤ ሆኖም ግራ ቀኙን መቃኘት ግን የግድ የሚል መሆኑንም ይኸው ወጣት አመልክቷል።
የጠ/ሚ/ሩ ከሁለት ወራት በላይ መሰወር፤ በኢትዮጵያ መነጋገሪያ መሆኑን፤ ሆኖም በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ጥቂቶች መሆናቸውን፤ የሲ. ኤን. ኤን. ዘጋቢ አመልክቷል።
ጀሚኒክስ ካሳዬ የተባለ የ30 ዓመት ወጣት በበኩሉ፤ “ጥቂቶች የሚከተለው ሁኔታ አስጨንቋቸዋል። ሌሎች ደግሞ በጠ/ሚ/ሩ ስንብት ደስተኞች ሆነዋል” ብሏል።
ወጣቱ ጀማኒክስ ካሳዬ፤ እሱም የጠ/ሚር መለስ ዜናዊን ስንብት እንደሚፈልግ ገልጿል። “እኔም እሳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ዴሞክራሲ የለም። ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት አልተከበረም። ምግብ የለም፤ ፍትህ የለም፤ ተጠያቂነት የለም።” በማለት ዘርዝሯል።
ሆኖም ጠ/ሚ/ሩ በዚህ መልክ መሰናበታቸው በሀገሪቱ ሌላ አምባገነን እንዲከተል የሚጋብዝ በመሆኑ፤ ምኞቱ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣናቸውን ሲለቁ ማየት እንደነበር አስተያየቱን ሰጥቷል።