ሲፒጄ የኦባማ አስተዳደር በመለስ ዜናዊ ላይ ጫና እንዲያደርግ ጠየቀ

ግንቦት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ( ሲፒጄ) ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በጻፈው ደብዳቤ፣ በአለማቀፉ የግብርና እና የምግብ ዋስትና መርሀግብር ላይ ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት አቶ መለስ ዜናዊ የፕሬስ ነጻነትን እንዲያከብሩ ግፊት እንዲደረግባቸው ጠይቋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው አፈና እየተባባሰ መምጣቱን የገለጠው ሲፒጄ፣ የባራክ ኦባማ መንግስት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ፣ አቶ መለስ ሰብአዊ መብቶችን እንዲያክብሩ ጫና እንዲያደርጉ ተማጽኗል። እንደ ሲፒጄ ሁሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም አቶ መለስ < ያለምንም ጥያቄ በስብሰባው ለመሳተፍ የይለፍ ወረቀት ማግኘታቸውን ” በመቃወም ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ደብዳቤ ጽፏል።

በሌላ ዜና ደግሞ ከኢትዮጵያውያን በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚተዳደረው፣ ይሁን እንጅ የገዢው ፓርቲ ልሳን በመሆን እነ አዲስ ራእይን ሳይቀር ማስናቅ የጀመረው፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችን ማስፈራራቱን ቀጥሎአል። አዲስ ዘመን “አንቀጽ 29፣የፕሬስ ቀንና ማተሚያ ድርጅት” በሚል ርዕስ “ስሜነህ” በተባሉ ጸሐፊ የተጻፈውን ጽሁፍ ይዞ ወጥቷል፡፡ ጽሁፋ ሚያዚያ 25 ቀን 2004 ፣ ወይም እኤአ ሜይ 3፣ 2012 በአፍሪካ ህብረት አዳራሸ የተከበረውን የፕሬስ ቀን አስታውሶ በዚህ መድረክ የፕሬስ አባላቱ
በማተሚያ ቤቶች ዘንድ ውል ፈርሙ መባላቸውን  ቅድመ ምርመራ ነው በሚል አጥብቀው መቃወማቸውን ኮንኖአል፡፡ተቋማቱ ጉዳዩ የህገመንግስት ጥሰት ነው ያሉትን በመጥቀስ ሚዲያው ህገ መንግስቱን የሚያስታውሰው
ሲነካ ብቻ ነው” ብሎአል።   አብዛኛዎቹ ስለህገመንግስቱ የሚዘምሩትና የሚጨነቁት ወይም ዕውቅና በመስጠት የሚከራከሩት እነርሱን የተመለከተ አጀንዳ በተፈጠረ ግዜና በየዓመቱ ሜይ 3   ላይ ነው፡፡”  የሚለው ጽሁፉ፣ ፍትህ ጋዜጣ ለበርካታ ግዜያት የጻፋቸውን በእየ ርእሳቸው ከጠቀሰ በሓላ ፣   ግንቦት 7 የተባለው አሸባሪ ቡድን ከጀርባ ሆኖ ጋዜጣውን በገንዘብ እየረዳው ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬውን አስፍሯል፡፡

አዲስ ዘመን ዛሬ“ የንግድ ውል የቅድመ ምርመራ ሕግ መሆን ይችላል?”  በሚል ርዕስ በአጀንዳ አምዱ ባወጣው ጽሁፍ ፣ በቅርቡ ማተሚያ ቤቶቹ ያቀረቡት ውል ተራ የንግድ ውል በመሆኑ ከቅድመ ምርመራና ከሕገመንግስቱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብሎአል።
የጹሑፎቹ ተከታትሎ መውጣት አሳታሚዎቹ ነገ ከብርሃንና ሰላም ጋር ላላቸው ስብሰባ አስቀድሞ የተሰጠ ምላሸ ሊሆን እንደሚችል የብዙ አሳታሚዎች ግምት ሆኗል።

ጽሁፉን የመንግስት ባለስልጣናት ወይም ለባለስልጣናት ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች እንደሚጽፉት ይገመታል። ከ20 በላይ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያ ያለው መንግስት፣ 99 ነጥብ 6 በመቶ በሆነ ደምጽ አሸንፉያለሁ የሚል መንግስት በጥቂት የመገናኛ ብዙሀን ዘገባ መርበትበት መጀመሩ ታዛቢዎችን እያስደመመ ነው። አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ጋዜጠኛ፣ መንግስት በ1997 ምርጫ ወቅት የነበሩ ጋዜጦች ፈጥረውት ከነበረው ድንጋጤ አለመውጣቱን መታዘብ ይቻላል ብለዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ “አኬልዳማ”በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ያስተላለፈውን ፕሮፓጋንዳ ያቀረበው ጋዜጠኛ ፍርድ ቤት ቀረበ።

ጋዜጠኛው ፦”እንዳነብ የተሰጠኝን አነበብኩ እንጂ፤ፕሮግራሙ የኔ አይደለም” ሲል ራሱን ተከላክሏል።

አንድነት ፓርቲ፦’ኢቲቪ አኬልዳማ በተሰኘው ፕሮግራሙ ስሜን  አጥፍቷል” በማለት በኢቲቪ እና በፕሮግራሙ አቅራቢ ጋዜጠኛ ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ጋዜጠኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ  በተላለፈው ውሳኔ መሰረት አብዲ ከማል የተባለው ይኸው የኢቲቪ ጋዜጠኛ ግንቦት 3 ቀን 2004 ዓመተ ምህረት በፌዴራል የመጀመሪያ  ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ፍትሀ-ብሔር ችሎት ቀርቦ በክሶቹ ጭብጦች ላይ ክርክር ተደርጓል።

አንደኛ ተከሳሽ ኢቲቪ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ፦” በዚህ ጉዳይ   ልከሰስ እንኳ የሚገባ ከሆነ በወንጀል እንጂ በፍትሐብሔር መሆን ስለሌለበት ፍ/ቤቱ ክሱን ውድቅ ያድርግልኝ” ሲል ሁለተኛው ተከሳሽ የኢቴቪ ጋዜጠኛ አብዲ ከማል ደግሞ፦” የዘጋቢ ፊልሙ አዘጋጅ እኔ ስላልሆንኩ፤ ልጠየቅ አይገባም” ሲል ክሱን ተቃውሟል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ጠበቃ አቶ ገበየሁ ይርዳው  ለኢቴቪ ተወካይ  በሠጡት መልስ፦” በፓርቲው ላይ የፈፀማችሁት የስም ማጥፋት በወንጀልና በፍትሐብሔር የሚያስጠይቅ ነው።  እኛ የመሠረት ነው ክስ የፍትሐብሔር ብቻ ነው”በማለት ክሱ በፍትሐ ብሔር የሚያስጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።.

አብዲ ከማል የተባለው የ አኬልዳማ ፕሮፓጋንዳ አቅራቢ  ያነሳውን የክስ መቃወሚያ  በተመለከተም፦ ዘጋቢ ፊልሙ ላይ አዘጋጅ ካለመጠቀሱ እና   አቅራቢው ራሱ ከመሆኑ አንፃር  ክስ ሊመሰረትበት እንደቻለ ጠበቃው አስረድተዋል።

“እኛ የምናውቀው አዘጋጅ እና አቅራቢ አብዲ ከማል የተባለ ጋዜጠኛ ነው”ሲሉም አቶ ገበየሁ አክለዋል።

ፍርድ ቤቱም  የ ኢቲቪን ነገረ-ፈጅ አቶ ተማም ሁሴንን ፦”የፕሮግራሙ አዘጋጅ ማነው?” በማለት የጠየቀ ሲሆን፤ እርሳቸውም፦”የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ነው”በማለት መልስ ሰጥተዋል።

 

በመጨረሻም መዝገቡን መርምሮ ምላሽ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለመጪው ግንቦት 10 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ፍኖተ ነጻነት ዘግቧል

የአኬልዳማ ፕሮፓጋንዳ አቅራቢ የሆነው  አብዲ ከማል ፦”የታዘዝኩትን አነበብኩ እንጂ ስለፕሮግራሙ የማውቀው የለም”በማለት ራሱን ከወንጀል ነፃ ለማድረግ ያደረገውን ሙከራ ያስተዋሉ የችሎቱ ታዳሚዎች፦” በመንግስት ሚዲያዎች ውስጥ ጋዜጠኛ መሆን ማለት፤ ግርድፉንም፣ቆሻሻውንም የነፉበትን ሁሉ እየተቀበለ እንደሚያስተላልፍ ቀዳዳ ወንፊት መሆን ነው ለሚባለው ነገር ይህ ጋዜጠኛ ጥሩ ምሳሌ ሆኗል”ብለዋል።

ጋዜጠኛው ፕሮፓጋንዳውን በሚያነብበት ጊዜ ይታይበት የነበረውን የድንጋጤ ገጽታ ያስታወሱት እነዚህ ታዳሚዎች፤ በባርነት ሰንሰለት ተተብትበው ያላመኑበትን እየሠሩ ያሉ የመንግስት ጋዜጠኞች ወደ ህሊናቸው ተመልሰው የጣሏትን ነፀነታቸውን እንዲፈልጓት መክረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide