መንግስት ዳኞቹ የህዝብ አመኔታ እንደሌላቸው አመነ

ግንቦት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፍትህ ሚንስትር ከሚያዚያ 10 ቀን እስከ ሚያዚያ 17 ቀን 2004 ዓ.ም “ለፍትህ ሥርዓቱ መጎልበት እንዘጋጅ” በሚል መርህ ሲያከብር ባከናወነው የዳሰሳ ጥናት ላይ የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ዳኞችና ዐቃቤያን ሕጎች በተገልጋዮች፣ በታዛቢዎችና ችሎቱን በሚታደሙ ሦስተኛ ወገኖች እምነት እንደማይጣልባቸው ማረጋገጡን የሚ/ር መሥሪያ ቤቱ ምንጮች አስታወቁ፡፡

በአንፃሩ በሌሎች ችሎቶች በሚታዩ ተራ የወንጀል ድርጊቶችና የአነስተኛ ባለሥልጣናት ሙስና ላይ የተሰማሩ ዳኞች፣ ዐቃቤያን- ሕጎች ግን የተሻለ አመኔታን በመጠይቁ- ግብረ-መልስ ( ፊድባክ) ላይ ማግኘታቸውንም ገልጸውልናል፡፡ 

በፌዴራል ደረጃ የፍትህ ሣምንትን ከሦስት ሣምንት በፊት ያከበረው ሚ/ር መሥሪያ ቤቱ የዳሰሳ ጥናቱን በኬዝ-ቲም ያሰራ ሲሆን አትኩሮቱም በፍርድ ቤቱ ለክርክር፣ ለመታዘብ እና የተለያዩ ጉዳዮችን ለማከናወን የመጡ ሰዎች መጠይቅ እንዲሞሉ አድርጓል ብለዋል፡፡

በመጠይቅ ወረቀት የተሰበሰበውን ግብረ- መልስ በመተንተን በተሰራው ጥናት ላይ የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች ሸምሱ ሲርጋጋ፣ ሙሉጌታ ኪዳኔ፣ እንዳሻው አዳነ፣ ሁሴን ይመር እና በሪሁን አራጋው በሽብርተኝነት፣ በሀገር መክዳት፣ እና ሁከት በመፍጠር በሚከሰሱ የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ ነፃ አሳቢያን ዜጎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የፍርድ ሂደት ላይ ነፃ ናቸው ተብለው በተገልጋዮችና በታዛቢያን ዘንድ ያልታሰቡ ሲሆን ፣ ዐቃቤያን- ህግ ዘረሰናይ ምስግናው፣ አንተነህ ጌታቸው፣ ብርሃኑ ወንድማገኝ እና ቴዎድሮስ … (ጫላ)? ደግሞ በግብረ- መልሱ ላይ የታማኝነት ደረጃቸው እጅግ ዝቅ ብሎ ተገኝቷል በማለት ለጥናት ወረቀቱ ኬዝ-ቲም ቅርበት ያላቸው የዜና ምንጫችን አስረድተዋል፡፡

በጥናቱ መሠረት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ እምነት ያጡ ዳኞችና ዐቃቤያን ሕግ ይለወጣሉ ወይ ሲል ዘጋቢያችን ላቀረበው ጥያቄ “አይመስለኝም” ያሉት ምንጫችን፣  ዳኞችን የሚመድበው የዳኞች ጽ/ቤት ሲሆን ተጠሪነቱም ለአቶ መለስ ዜናዊ ነው ብለዋል፡፡

ዳኛ እንዳሻው አዳነ በአሁኑ ጊዜ በአንዱአለም አራጌ የክስ መዝገብ የተከሰሱትን በመሀል ዳኝነት በማስቻል ላይ የሚገኙ ናቸው። ዳና ሸምሱ ሲርጋጋ ደግሞ በጭካኔያቸው እና የህወሀት ተለጣፊና ነገረፈጅ በመሆን ይታወቃሉ።  ዳኞችን ለመገምገም ለህዝቡ የቀረቡትን ጥያቄዎች በድረገጻችን መመልከት የምትችሉ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide