ሐምሌ ፲፯ ( አሥራ ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለ51 ዓመት ለባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ሲያገለግል የነበረው አንጋፋ ዳቦ ቤት አቶ ዳንኤል ለተባሉ የህውሃት ቀኝ እጅ ለካሬ ሜትር በብር 3600 ሂሳብ ተላልፎ መሰጠቱና በዚህም ምክንያት በህዝቡና በአመራሩ መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ሲያስነሳ ቆይቷል። የሃጂ ኣድጎአይ ዳቦ ቤት ላይ በህይወት በሌሉት የከተማዋ ባለውለታ ስም ልጆቻቸው ግንባታ ለማከናወን ለካሬ ሜትር በብር 3900 ዋጋ ቢያቀርቡም የበላይ አካላት በመከልከላቸው በእንጥልጥል ላይ ቆይቷል፡፡
ባህር ዳር ከተማ በወንዶች ፀጉር ስራ ለሚተዳደረው የህውሃት ቀኝ እጅ አቶ ዳንኤል በባህር ዳር ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት በመመሪያውና ደንቡ መሰረት ቤቱን በክራይም ቢሆን ለ51 ዓመት ለያዙት የሃጂ ኣድጎአይ ቤተሰቦች ይገባል በሚል በመወሰኑ ዙሪያውን በከበቡት የአገዛዙ ጠበቆች አማካኝነት በፌደራል ፍርድ ቤት ይግባኝ በማቅረብ በትዕዛዝ አስወስኗል።
ግለሰቡ በባህር ዳር ከተማ በነበረው አነስተኛ የወንዶች ጸጉር ቤት ሽፋን ይተዳደር የነበረ ሲሆን ፤ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውበት ማሰልጠኛ በሚል ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
ግለሰቡ ቦታውን በ4 ሚሊዮን ብር አየር ባየር እንደሸጠው መረጃ በማግኘታቸው በሰፈነ ሰላም ቀበሌ የሚገኙ የህዝብ ተቆርቋሪ አመራሮች ቅሬታ ቢቀርብበትም ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወሰድበት መቅረቱን ጥቆማውን ያቀረቡት አመራሮችም እንግልት እንደደረሰባቸው የውስጥ አዋቂዎች ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳንኤል የህውሃት ቀኝ እጅ እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን፣ ከ2000 ዓም በፊት ምንም ዓይነት ህብትም ሆነ ንብረት የሌለው በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ ዜሮ አራት በጸጉር ማስተካከል ስራ የሚሰራ ግለሰብ ቢሆንም በተለይ የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሰልል የህውሃት መንግስት በፕሮቶኮል ስም ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ ሌሎችን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጸጉር በማስተካከል ሲሰራ እንደነበር ታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ከቦታው ታሪካዊነት አንጻር ለ51 ዓመት ሲገለገሉበት ለቆዩት የሓጅ አድጎይ ቤተሰቦች ለመስጠት ቢሞክሩም የግንባታ ፈቃድ የተሰጠው አቶ ዳንኤል 3 አማራጮች ቢሰጡትም በእምቢተኝነት በመጽናቱ ቦታውን ለማስረከብ በአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ኢንስፔክተር ክንፈ አማካኝነት ቅዳሜ በ15/11/09 ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት ታጅቦ ቤቱ መፍረሱን ለማወቅ ተችሏል።
ባህር ዳርን ስናስብ ለዘመናት አብሮ ስማቸው የሚነሳው ታሪካዊ አባ አድጎይ ዳቦ ቤት ለአቅመ ደካሞች፣ ለከተማዋ ጎዳና ተዳዳሪዎችና ጎልማሶች ከስፖርት ሲመለሱ ዳቦ በነጻ በማደል ይታወሳል፡፡