ሱዳንና ግብጽ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠንከር ተስማሙ

ጥር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግብጹ ወታደራዊ አዛዥ እና የአገሪቱ መሪ ማርሻል አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር አብደል ራሂም ሙሃመድ ሁሴን ጋር ወታደራዊ ግንኙነቱን ለማጠንከርና የጋራ ድንበሮቻቸውን ለመጠበቅ መስማማታቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።

ሚኒስትር ሁሴን ካይሮ በመሄድ የግብጹን ወታደራዊ መሪ ያገኙ ሲሆን፣ ሁለቱ አገራት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

የሱዳኑ ወታደራዊ አዛዥ እንደገለጹት ሁለቱ መሪዎች በአካባቢው ስላለው የጸጥታ ሁኔታም ተነጋገረዋል። የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያ የምትገነባውን የአባይ ድልድይ በመደገፏ የግብጽ ባለስልጣናትን ማስቆጣቱ ይታወቃል። የሁለቱ አገራት አዲስ ግንኙነት የሱዳን መንግስትን አቋም ያስለውጥ አያስለውጥ የታወቀ ነገር የለም። ሁለቱ አገራት ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ መወሰናቸው ለኢትዮጵያ መንግስት መልካም ዜና ላይሆን እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ።